
ከ 6 ሰአት በፊት
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን በተመለከተ መከተል ስላለባት ፖሊሲ የሚመክር ስብሰባ ሐሙስ ኅዳር 20/2016 ዓ.ም. አድርጓል።
ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ገደማ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ አካባቢው ሲመላለሱ የከረሙት አምባሳደር ማይክ ሐመር ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጀት ዩኤስኤአይዲ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳዳሪ የሆኑት ታይለር ቤክልማንም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምትሰጠው የእርዳታ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
ለአንድ ሰዓት ከ15 ደቂቃ ገደማ በቆየው ምስክርነት በተሰማበተ ስብሰባ ላይ የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን፣ የአማራ እና ትግራይ ክልል የሰላም ሁኔታን እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦትን የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ ባለፉት ጥቂት ወራት በኢትዮጵያ እና በአካባቢው አገራት መነጋገሪያ ሆኖ በሰነበተው የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ጉዳይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ጋር ተያይዞ ተነስቶ ነበር።
ስለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምን ተባለ?
የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ በመጀመሪያ የተነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላቸውን ትችት በጠንካራ ቃላት ካቀረቡት በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ስር የሚገኘው የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆን ጄም ነው።
ሰብሳቢው፤ በውይይቱ ላይ የመጀመሪያ የሆነውን ጥያቄ ሲያቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ መናገራቸውን እና የባሕር በር አለመኖር ወደፊት ሊከሰት ለሚችል ግጭት ስጋት መሆኑን መጥቀሳቸውን አንስተዋል።
“ስለጉዳዩ ይበልጥ በተረዳሁ ቁጥር የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ፍላጎት የለውም የሚለው ስጋቴ እየጨመረ ነው” ሲሉ ይህ ሁዳይ በአካባቢው ያለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
አክለውም፤ የባሕር በር አለመኖር ወደፊት ሊከሰት ለሚችል ግጭት ስጋት ነው የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር “ማስፈራሪያ ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አምባሳደር ማይክ ሐመር፤ የወደብ ጥያቄን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው አስተያየት በአሜሪካ እና በቀጣናው ባሉ አገራት ላይ ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄን ለመመለስ ያሰበችው በሰላማዊ እና በንግድ አማራጭ እንደሆነ መናገራቸውን ጠቅሰዋል።
- “የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ14 ጥቅምት 2023
- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እና የፈጠረው ስጋት21 ጥቅምት 2023
- ‘ውጥረትን የሚያቀጣጥለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀይ ባሕር ወደብ የማግኘት ፍላጎት’8 ህዳር 2023
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በመጠየቅ የሚታወቁት ብራድ ሸርማን የተባሉት የምክር ቤት አባል በተመሳሳይ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ይህንን ጉዳይ አንስተውታል።
የኢትዮጵያ የባሕር ወደብ ለማግኘት ስላላት ፍላጎት ንግግር እንዳለ የጠቀሱት እኚህ የምክር ቤት አባል፤ “መቼም. . . የዓለም አቀፍ ድንበርን እንደማንቀይር ይታወቃል” ብለዋል።
ይሁንና ወደብ አልባ አገራት ወደብ የማግኘት እና ያለ ክፍያ የመጠቀም መብት አላቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። በዚህ አግባብ ቦሊቪያ የቺሊን ወደብ በተመለከተ “የተወሰነ መብት አላት” ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለምስክርነት የተቀመጡት አምባሳደር ማይክ፣ ከዚህ ቀደም በቦሊቪያ እና በቺሊ ማገልገላቸውን ጠቅሰው የሁለቱ አገራት ጉዳይ መነሳቱን ትኩረታቸውን እንደሳበው ጠቅሰዋል። በሐሙሱ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋጋራቸውን አንስተዋል።
አምባሳደር ማይክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይኸው ወደብ የማግኘት ጉዳይ መሆኑን ለምክር ቤት አባሉ ብራድ ሸርማን ተናግረዋል። በዚህ ንግግር ወቅትም ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ የቦሊቪያ እና የቺሊን ጉዳይ በምሳሌነት እንድትመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመልከታቸውን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

የቦሊቪያ እና ቺሊ የባሕር በር ውዝግብ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በምሳሌነት ያነሱት የቦሊቪያ እና የቺሊ የባሕር በር ውዝግብ በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ለአምስት ዓመታት ክርክር የተደረገበትን ጉዳይ ነው።
ጎረቤታሞቹ ቦሊቪያ እና ቺሊ በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ አገራት ናቸው። ቺሊ 18.4 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ሲኖራት፤ በቆዳ ስፋት የምትበልጠው ቦሊቪያ ደግሞ 12 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛለች። ቺሊ፤ ከደቡብ አሜሪካ አገራት መካከል ሀብታም እና የተረጋጋች ስትሆን፣ ቦሊቪያ ደግሞ የተለያዩ ተፎካካሪ ፍላጎቶች የሚስተዋሉባት አገር ናት።
ሁለቱ አገራት ሌላም የሚያለያያቸው ጉዳይ አለ። በፓሲፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ የተዘረጋችው ቺሊ የተለያዩ ወደቦች ባለቤት ነች። ቦሊቪያ ደግሞ በተቃራኒው የባሕር በር የናፈቃት ወደብ አልባ አገር ናት።
ሰንደቅ ዓላማዋ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ የሆነው ቦሊቪያ የባሕር በር አልባ የሆነችው ከመጀመሪያው አንስቶ አልነበረም። ቦሊቪያ 400 ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተዘረጋውን የባሕር ዳርቻዋን ያጣቸው ከዘመናት በፊት በተካሄደ ጦርነት በቺሊ ከተሸነፈች በኋላ ነው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተካሄደው ይህ ጦርነት ሲጠናቀቅ አሸናፊዋ ቺሊ የቦሊቪያ ግዛት የሆነ 120 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን መሬት ቆርሳ ወሰደች። ቦሊቪያን ከፓሲፊክ ውቅያኖስ ያገናኝ የነበረው ይህ መሬት ስፋቱ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተደምረው ያክላል።
ከጦርነቱ ማብቃት 20 ዓመታት በኋላ ሁለቱ አገራት ባደረጉት ስምምነት ወደብ አልባ የሆነችው ቦሊቪያ፣ የቺሊን ወደብ እንድትጠቀም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ይሁንና ቦሊቪያውያን የተወሰደባቸውን መሬት እና የባሕር በርን የማስመለስ ጥያቄን አልተዉትም። ወደብ አልባ ሆነው እንኳ በየዓመቱ የባሕር ቀንን ያከብራሉ።
ሁለቱ አገራት በባሕር በር ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሻክሮ ለረጅም ጊዜ ከቆዩ በኋላ የቀድሞው የቦሊቪያ ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌስ ውዝግቡን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ አደረጉት። የአገራቸው ኢኮኖሚ በሚፈለገው መጠን ላለማደጉ ወደብ አልባነትን ምክንያት በማንሳት “የባሕር በር እንድናገኝ ሲባል ቺሊ ለድርድር የመቀመጥ ግዴታ አለባት” አሉ።
እንዲህ ብለውም ብቻ ቁጭ አላሉም። እአአ በ2013 ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት አቤት አሉ። በዓመቱም በ200 ገጾች የተዘጋጀውን የአገራቸውን አቤቱታ ራሳቸው ይዘው ወደ ኔዘርላንዷ ሄግ ከተማ በማምራት መዝገብ አስከፈቱ።
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት “ይህንን ጉዳይ የማየት ሥልጣን አለው ወይ?” ከሚለው ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ክርክር ተደርጎበታል። ቺሊ እአአ 1904 የተፈረመውን የሁለቱን አገራት ስምምነት ስትጠቅስ፤ ቦሊቪያ ደግሞ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን መብት በማንሳት በክርክር ቆዩ።
በጥቅምት መጀመሪያ ላይ 2018 ግን ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ አሳለፈ። ይህ ውሳኔ ታዲያ የቦሊቪያውን ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌስን እና ውሳኔውን በተለያዩ ከተሞች በተሰቀሉ ትላልቅ ስክሪኖች በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩትን ቦሊቪያውያን ያስደሰተ አልነበረም።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት፤ “ቦሊቪያ የባሕር በር እንድታገኝ ሲባል ቺሊ ድርድር የመቀመጥ ግዴታ የለባትም” ሲል ወሰነ። ጉዳዩን ከተመለከቱት 12 የፍርድ ቤቱ ዳኞች መካከል የቦሊቪያን ጥያቄ የደገፉት ሦስቱ ብቻ ነበሩ።
ይህ የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳሪ ነው።

ምን አማራጭ አለ?
የቦሊቪያ እና የቺሊ ውዝግብ ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተነሳበት በሐሙስ ዕለቱ የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የቦሊቪያን ጥያቄ እንደሚደግፉ የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ ብራድ ሸርማን ለኢትዮጵያም ጥያቄ መፍትሄ ያሉትን ጠቁመዋል።
“ኤርትራ የትኛውም ግዛቷን ለመስጠት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ወደቧን ስትጠቀም ምንም ዓይነት ክፍያ ላለማስከፈል ብትስማማ ለሰላም አንድ እርምጃ ይሆናል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ማይክ ሐመር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄውን ለማሳካት ያቀደው ሰላማዊ በሆነ የንግድ [ሰጥቶ በመቀበል] መንገድ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግልጽ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የአሜሪካ መንግሥት ይህንን መንገድ እንደሚያበረታታ የጠቀሱት ልዩ መልዕክተኛው፤ “በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሌላ ጦርነት ማስተናገድ አንችልም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ለሦስት አስርት ዓመታት ጦርነት በኋላ ኤርትራ ነጻ አገር ስትሆን ወደ ብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በድንበር ይገባኛል ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ለገቢ እና ለወጪ ንግድ እንቅስቃሴዋ በጂቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ከሆነች ሰለሳ ዓመታት አልፈዋታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻሉ በማድረግ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አግኝተዋል። ኢትዮጵያም የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀም የምትችልበት ዕድል ሲመቻች ቆይቷል።
ቀደም ባለው አስተዳደር የኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት ጉዳይ የተዘጋ ጉዳይ ተደርጎ ከቆየ በኋላ ባለፉት ጥቂት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወደብ ባለቤትነት ጉዳይን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተው በተለያዩ መድረኮች ላይ መናገራቸው በአካባቢው ስጋት ፈጥሯል።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ጦርነትን ከማንሳት ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ እንደሌለ በተደጋጋሚ ከመግለጻቸው ባሻገር፣ ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የአገሪቱን ግዙፍ ተቋማትን በመጋራት ሰጥቶ በመቀበል እና በንግግር የሚሆን ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።
ከዚህ አንጻርም በኢትዮጵያ እና በአጎራባቾቿ ባለወደብ አገራት ምን አይነት ግንኙነት እየተካሄደ እንደሆነ አስካሁን የተሰማ ነገር የለም።