
ከ 4 ሰአት በፊት
በአሜሪካዋ ጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የእሰራኤል ቆንስላ ጽህፈት ቤት በር ላይ አንድ ግለሰብ ተቃውሞውን ለመግለጽ እራሱን በእሳት በማቃጠሉ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ “አደገኛ ፖለቲካዊ ተቃውሞን የመግለጫ መንገድ” ብሎ የገለጸውን ድርጊት የፈጸመው ሰው ማንነት ባይገለጽም ከእስራኤል ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውጪ ነዳጅ እና የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማን ይዞ እንደነበረ ተገልጿል።
ግለሰቡ እራሱን በእሳት ባቃጠለበት ወቅት ለማስጣል የሞከረ በስፍራው የነበረ አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ላይ በእጁ እና በእግሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የአትላንታ የእሳት አደጋ መከላከያ ባለሥልጣን ሮድሪክ ስሚዝ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከክስተቱ በኋላ በተቃውሞ እራሱን በእሳት ያቃጠለው እና ለማስጣል የሞከረው የጥበቃ ሠራተኛ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በደቡባዊ ምሥራቅ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የእስራኤል መንግሥት ወኪል የሆነው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አናት ሱልጣን-ዳዶን ባወጡት መግለጫ ከቢሯቸው ደጃፍ ላይ በተከሰተው ሁኔታ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም “በእስራኤል ላይ የሚደረግ ጥላቻ እና ትንኮሳ በዚህ አይነቱ ዘግናኝ ሁኔታ መገለጹ በጣሙን ያሳዝናል” ካሉ በኋላ አደጋውን ለማስቆም ሲል ለተጎዳው የጥበቃ ሠራተኛ መልካሙን ተመኝተዋል።
- የሕዝባቸውን ሰቆቃ በርቀት ሆነው እየተጋፈጡ ያሉት ፍልስጤማዊ አሜሪካውያን26 ህዳር 2023
- በጋዛ 100 ሺህ የሚጠጉ ሕንፃዎች ሳይወድሙ እንዳልቀሩ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችከ 7 ሰአት በፊት
- ሐማስ ከእስራኤል አፍንጫ ስር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ እንዴት ኃይሉን መገንባት ቻለ?29 ህዳር 2023
ሁለት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደው ውጊያ በተደረሰ ጊዜያዊ የትኩስ አቁም ስምምነት አማካይነት ለሳምንት ያህል ጋብ ካለ በኋላ ትናንት አርብ ጠዋት መልሶ ተጀምሯል።
ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎችን ሲገድል፣ 240 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደው ነበር። ከመካከላቸው የተወሰኑት የተኩስ አቁም በተደረገበተ ጊዜ ተለቀዋል።
በተመሳሳይ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ አሰካሁን ደረስ ወደ 15,000 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒሰቴር አስታውቋል።
በዚህ ጦርነት እስራኤላውያንን እና ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ የተለያዩ ሰልፎች በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ተካሂደዋል።
ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ በአሜሪካ ውስጥ እስራኤላውያንን የሚቃወሙ ፀረ ሴማዊ እና ፍልስጤማውያንን የሚቃወሙ ፀረ ሙስሊም የሆኑ የጥላቻ ንግግሮች መበራከታቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ካሊፎርኒያ ውስጥ በተካሄደ እስራኤልን እና ፍልስጤምን በሚደግፉ ሰልፈኞች መካከል ግጭት ተከስቶ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪን አስሯል።
የ69 ዓመቱ ሟች አዛውንት ማርቲን ኬስለር ሰልፈኞቹ መካከል ግጭት በተከሰተበት ወቅት ወድቀው የነበረ ሲሆን፣ ሕይወታቸው ያለፈው ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ኢሊኖይ ግዛት ውስጥ አንድ ግለሰብ የስድስት ዓመት ታዳጊን በጥላቻ ተነሳስቶ በስለት ወግቶ በመገደለ ተይዞ ተከሷል።
