
ከ 6 ሰአት በፊት
የአደገኛ የወንጀለኞች ቡድን አባል የነበረ እስረኛ በጆርድ ፍሎይድ ግድያ የታሰረውን የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪንን 22 ጊዜ በስለት በመውጋት ክስ ተመሠረተበት።
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ፣ ጆን ቱርሳክ የተባለው እስረኛ ባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 14/2016 ዓ.ም. ላይ አሪዞና በሚገኘው የፌደራል እስር ቤት ውስጥ እራሱ በሠራው ስለት የቀድሞ የፖሊስ አባል የነበረውን ሾቪንን 22 ጊዜ እንደወጋው አመልክቷል።
ሾቪን በጥቃቱ ምክንያት ሕይወቱ ባያልፍም ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጎ ሆስፒታል መግባቱ ተዘግቧል።
የሚያኒያፖሊስ ግዛት የፖሊሰ መኮንን የነበረው ዴሪክ ሾቪን ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድ በመግደል ጥፋተኛ ተብሎ ከ40 ዓመት በላይ ተፈርዶበት የእስር ላይ በሚገኝበት ጊዜ ነው ጥቃቱ የተፈጸመበት።
ዴሪክ ሾቪን የፈጸመው ግድያ በአሜሪካ ውስጥ የፖሊስ የጭካኔ ድርጊቶችን እና ዘረኝነትን በመቃወም በመላው አሜሪካ ለተቀሰቀሱት መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች መነሻ ምክንያት ሆኖ እንደነበረ ይታወሳል።
- የጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች31 ግንቦት 2020
- ዓለምን ያናወጠውን ቪዲዮ የቀረጸችው ታዳጊ፡ ሰው ሲገደል መቅረጽ፤ ጽድቅ ነው ኩነኔ?15 ሰኔ 2020
- በአሜሪካው ተቃውሞ ንብረታቸው የወደመባቸው ኢትዮጵያዊያን12 ሰኔ 2020
የቀድሞው የሜክሲኮ የማፊያ ቡድን አባል የነበረው ቱርሳክ በቀድሞው የፖሊስ አባል ሺቪን ላይ የግድያ ሙከራውን የፈጸመው በምሳ ሰዓት በእስር ቤቱ ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ እንደነበር ተገልጿል።
ቱርሳክ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በሰጠው ቃል ሾቪን ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት እስረኛ በመሆኑ እርሱን ለመግደል ለወራ ያህል ሲዘጋጅበት እንደቆየ ተናግሯል።
የፍርድ ቤት ሰንዶች እንዳመላከተቱት የእስር ቤት ኃላፊዎች ጥቃቱን ለማስቆም ፈጣን እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ ቱርሳክ እስረኛውን የመግደል ዕቅድ ነበረው።
የ52 ዓመቱ ቱርሳክ ሾቪን ላይ የግድያ ሙከራውን አርብ ቀንን ጠብቆ የፈጸመው ለጥቁሮች መብት እና ክብር የሚቆረቆረው ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ የሚባለው እንቅስቃሴ እንዲሁም የሜክሲኮ ማፊያ ቡድን ከአርብ ቀን ጋር ቁርኝነት ስላላቸው ነው ብሏል።
ነጭ ዝርያ ያለው ቱርሳክ እአአ 2001 ላይ የኤፍቢአይ መረጃ ሰጪ ሆኖ ሳለ ወንጀሎችን በመፈጸሙ የ30 ዓመታት እስር እንደተፈረደበት ሎስ አጀንለስ ታይምስ ዘግቧል።

በእስረኛው በተደጋጋሚ በስለት ተወግቶ ከባድ ጉዳት የደረሰበት የቀድሞው የፖሊስ አባል ዴሪክ ሾቪን ለእስር የተዳረገው፣ ከሦስት ዓመት በፊት ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን መሬት ላይ አስተኝቶ አንገቱ ላይ በጉልበቱ በመርገጥ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በላይ ከያዘው በኋላ ሕይወቱ በማለፉ ነው።
ይህንን ክስተት በአካባቢው የነበረች አንዲት ወጣት በስልኳ ካሜራ ቀርጻ ካሰራጨችው በኋላ ፖሊሶች በሚፈጽሙት ዘር ተኮር በደል ላይ ከአሜሪካ ባሻገር በመላው ዓለም ቁጣ እና ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በዚህ ድርጊት ለእስር የተዳረገው ሾቪን ከፍሎይድ ግድያ ጋር በተያያዘ በቀረቡበት ክሶች የ22 ዓመት አስር የተፈረደበት ሲሆን፣ በማስከተል ደግሞ የሟቹን መብት በመጣስ ተጨማሪ የ20 ዓመት እስር ተበይኖበታል።
ዴሪክ ሾቪን ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር በተያያዘ ፍትሃዊ የሆነ ፍርድ አላገኘሁም በማለት በቅርቡ ቅሬታ ቢያቀርብም የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታውን ውድቅ አድርጎበታል።
