
ከ 7 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ አገራት የሚገኙ መንገደኞቹ በስፋት የሚጠቀሙባቸወ ‘ጋና መስት ጎ’ በሚል መጠሪያ የሚታወቁትን ሻንጣዎች ከበረራዎቹ ማገዱን አስታወቀ።
የአየር መንገዱ የናይጄሪያ ቢሮ እንደገለጸው አብዛኛውን ጊዜ በነጋዴዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውሉት እነዚህ ዕቃ መሸከፊያ ሻንጣዎች የአየር ማረፊዎችን የዕቃ ማንቀሳቀሻ ማሽኖችን ለብልሽት እየዳረጉ በመሆናቸው ክልከላውን መጣሉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ ክልከላው የተላለፈው ሻንጣዎቹ “በበርካታ አየር ማረፊያዎች የሻንጣ ማስረከቢያ ማሽኖች (ኮንቬየር ቤል) ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ” አየር መንገዶችን ከፍተኛ ወጪ እያስወጡ በመሆናቸው እንደሆነ አመልክቷል።
እነዚህ የመንገደኞች ጓዝ መሸከፊያ ሻንጣዎች ‘ጋና መስት ጎ’ የሚለውን ስያሜያቸውን ያገኙት እአአ 1980ዎች አብዛኞቹ ጋናውያን የሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ከናይጄሪያ በተባረሩ ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ ውለው ስለነበረ ነው።
የተባረሩት ስደተኞች ባለ ቀይ እና ሰማያዊ ቀለም ሻንጣዎችን በጀርባቸው አዝለው ነበር ናይጄሪያ በወቅቱ ለቀው የወጡት።
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስን ጨምሮ 31 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማማ14 ህዳር 2023
- በአፍሪካ አየር ላይ ‘የአንበሳውን ድርሻ’ እየያዘ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 19 ሀምሌ 2022
- አፍሪካን እና አፍሪካውያንን ብዙ እያሳጣቸው ያለው እጅግ ውዱ የአየር ቲኬት ዋጋ12 ሀምሌ 2023
እነዚህ ባዷቸውን በቀላሉ ተጣጥፈው ለመያዝ ቀላል የሆኑት የእቃ መያዣ ሻንጣዎች ከአፍሪካ በተጨማሪ በሌሎች አገራትም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ በተለያዩ አየር ማረፊያዎች ውስጥ ማየት የተለመደ ነው።
ሻንጣዎቹ ‘ጋና መስት ጎ’ ከሚለው መጠሪያቸው በተጨማሪ በዚምባብዌ ‘ቦትስዋና ባግስ’ ተብለው የሚታወቁ ሲሆን ኬንያውያን ደግሞ ‘ናይጄሪያ ባግ’ ብለው ይጠሯቸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህ ሻንጣዎች በካርቶን ውስጥ እንዲገቡ ከተደረገ ወይም በሌላ ጠንካራ መሸፈኛ በአራት ማዕዘን ቅርጽ በአግባቡ ከታሸጉ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ሲልም በመልዕክቱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ጨምሮ በአፍሪካ በርካታ መደረሻዎች ያሉት ሲሆን መነሻውን በናይረጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ አድርጎ በናይጄሪያ የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎትም ይሰጣል።
እነዚህን የመንገደኞች ሻንጣዎች በአየር ማረፊያዎች ውስጥ እየተሽከረከሩ የመንገደኞችን ጓዞች በሚያስረክቡት ማሽኖች ላይ ብልሽት በማስከተላቸው ምክንያት ከዚህ ቀደምም በሌሎች አየር መንገዶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ታግደው ነበር።
እአአ 2017 ላይ የኔዘርላንድስ ኬኤልኤም እና የፈረንሳይ ኤርፍራንስ ሻንጣዎቹ በጓዝ ማስረከቢያ ሥርዓታቸው ላይ ችግር እያስከተሉ ነው በማለት ክልከላ ጥለዋል።
በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጄሪያን ጨምሮ በበርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠቃሚዎችን የሚያገለግል ሲሆን፣ በአካባቢው ባሉ አገራት አየር መንገዶች ላይም ከፍተኛ ድርሻ አለው።