ከፍርስራሾች መካከል የምትታይ ፍልስጤማዊ ታዳጊ

ከ 7 ሰአት በፊት

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ከመጀመሩ በፊት ቢቢሲ ያገኛቸው አዳዲስ የሳተላይት ምስሎች በሰሜን ጋዛ የደረሰውን ከፍተኛ የውድመት መጠን የሚያሳዩ ናቸው።

የሳተላይት ምስሎቹ የተነሱት የእስራኤል ጦር ለሳምንታት ሲያካሂድ የነበረውን የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ በተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ከመቆሙ በፊት ነበር። ሌላ የሳተላይት መረጃ ትንተናም በጋዛ የደረሰውን ውድመት አቅርቧል።

ከድሮን የተገኙ እና የተረጋገጡ የቪዲዮ ምስሎችም ሕንፃዎች እና መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን ያሳያሉ። ሰሜናዊ ጋዛ የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሆና ከፍተኛ ጉዳት ብታስተናግድም፣ ጉዳቱ ግን ለጠቅላላው የጋዛ ሰርጥ ተርፏል።

ጋዛ

የጋዛ ሰርጥ ዋና ከተማን የሚያጠቃልለው ሰሜናዊ ጋዛ “የሐማስ የስበት ማዕከል” እንደነበረች እስራኤል ገልጻለች። ጥቃቱ የሐማስ አዛዦችን እና ተዋጊዎችን በተሳካ ሁኔታ ዒላማ ማድረጉን እስራኤል ገልጻ፣ ቡድኑ ሲቪሎች ውስጥ ተደብቋል ብላ ከሳለች።

የሳተላይት መረጃ ትንተናዎች እንደሚያመለክቱት በጋዛ ሰርጥ ወደ 98 ሺህ የሚጠጉ ሕንፃዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል። አብዛኞቹ ጉዳት ደረሰባቸው ደግሞ በሰሜን ጋዛ የሚገኙት ናቸው።

የመረጃው ትንተና የተካሄደው በኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቨርስቲ ባልደረባው ኮሪ ሼር እና በኦሪገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጃሞን ቫን ዴን ሆክ ነው። ትንተናው በሁለት ምስሎች ንጽጽር ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም በሕንጻዎቹ ቁመት ወይም መዋቅር ላይ የተፈጠሩ ለውጦችን ከግምት አስገብቷል።

ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የበርካታ አካባቢ የሳተላይት ምስሎች ተተንትነዋል።

የአየር ጥቃቱ ጅማሬ ዒላማዎች

በጋዛ ሰርጥ በሰሜን እና በሰሜን ምሥራቅ የሚገኙት የቤት ላሂያ እና የቤት ሃኖን ከተሞች ከመስከረም 26ቱ የሐማስ ጥቃት በኋላ፣ የአየር ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) አካባቢው የሐማስ መደበቂያ መሆኑን ገልጿል።

ለእስራኤል ድንበር ቅርብ የሆነውና የወይራ ዛፎችን እና የአሸዋ ክምር የሚታይበት የቤት ላሂያ አካባቢ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሯል። ከታች የምትመለከቱት የሳተላይት ምስል በሰሜን-ምሥራቅ ቤት ላሂያ የሚገኝ ቦታን ያሳያል።

ጋዛ

ቡልዶዘሮች በፍርስራሹ ውስጥ መንገዶችን የጠረጉ ይመስላል። የእስራኤል ጦር አካባቢውን በማጽዳት በዙሪያው የመከላከያ ምሽጎችን አዘጋጅቷል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውን እና ከድንበሩ ከ1.6 ኪሎ ሜትር ርቃ ያለችውን ቤት ሃኖንም መትቷል። በመጀመሪያ ቀን የአየር ድብደባ በአካባቢው 120 ዒላማዎች መመታታቸውን አስታውቋል።

ጋዛ ሰርጥ

ከላይ ያሉት ምስሎች እንደሚያሳዩት ከጥቅምት 3 እስከ ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በርካታ ወለል ያላቸው ሕንፃዎች እና መስጊድ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

ዒላማ የሆነው ሆቴል እና አጎራባቾቹ

በጋዛ ላይ ከተፈጸመው የሳምንታት የአየር ጥቃት በኋላ፣ እስራኤል የምድር ጦር ሲገባ ታንኮች እና ቡልዶዘሮች ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች እያለፉ ነው የገቡት። ጦሩ በጋዛ ከተማ አካባቢ ወደሚገኘው ሻቲ የስደተኞች ካምፕ ወደ ደቡብ አቅጣጫ አምርቷል።

ከታች ያለው ምሥል እንደሚያሳየው በአንድ ወቅት የመኖሪያ አካባቢ በነበሩት አካባቢዎች በርካታ ጉድጓዶች ይታያሉ።

የጋዛን የመጀመሪያ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አል-ማሽታልን ጨምሮ ጎጆዎችን እና ሬስቶራንቶችን በያዘው የባሕር ዳርቻ አንዳንድ ሕንፃዎች በከፊል የወደሙ ይመስላሉ።

ጋዛ

የደቡብ ጋዛ የሳተላይት ምሥሎች

የአየር ጥቃቱ ከተጀመረ ከአንድ ሳምንት በኋላ የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ዋዲ ጋዛ ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዲሸሹ አስጠንቅቋል።

ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጋዛ ከተማን ለቀው ቢሰደዱም፣ ጦሩ በደቡብ አካባቢዎችም ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል።

ጋዛ

የስደተኛ መጠለያዎች ወድመዋል

በመካከለኛው ጋዛ የሚገኘው የኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ከመጀመሩ በፊት በተደጋጋሚ ተመቷል። መጠለያው ወደ 85 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ይኖሩበት እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ጋዛ ሰርጥ
ጋዛ ሰርጥ

ባለፉት ጥቂት ቀናት በበይነ መረበ በተሰራጨው እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው በዚህ ቪዲዮ ላይ ሰዎች ከወደሙ ሕንፃዎች ፍርስራሽ እቃዎችን ሲሰበስቡ ታይተዋል።

ከመጠለያ ጣቢያው በስተሰሜን የሚገኘው የጋዛ የኃይል ማመንጫ የተለመደውን ጥቁር ጭስ ሲያወጣ ከበስተጀርባ ይታያል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጠው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ጠይቋል።

በእስራኤል ትዕዛዝ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ወደ ደቡብ ጋዛ ሸሽቷል

በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው በኻን ዩኒስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በድንኳን ውስጥ ወይም በቦምብ በወደሙ ሕንፃዎች ፍርስራሽ ውስጥ ይኖራሉ።

ምንም እንኳን ጉዳቱ እንደ ሰሜኑ ክፍል ከፍተኛ ባይሆንም፣ በከተማዋ እስከ 15 በመቶ የሚደርሱ ሕንፃዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን እንደሚችል የኮሪ ሼር እና የጃሞን ቫን ደን ሁክ ትንታኔ ያሳያል።

በተኩስ አቁም ፋታው ወቅት የአየር ድብደባው ጋብ ሲል አንዳንድ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለሸመት ወጥተዋል። ከታች በምስሉ ላይ የሚታው የወደመ ሕንፃ በከተማው ታላቁ መስጊድ አካባቢ ይገኛል።

ጋዛ ሰርጥ

እስራኤል ለረዥም ጦርነት ራሷን አዘጋጅታለች

የእስራኤል ወታደሮች ከሰሜን ጋዛ ወደ ታች በመዝለው የጋዛን ሰርጥን ወደ ምዕራብ በመቁረጣቸው የጋዛ ከተማን ከደቡባዊ ክፍል ለይተውታል።

ከዚህ በታች ያለው ምስል በጋዛ ከተማ በስተደቡብ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በርካታ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ ነበር።

በእስራኤል ጦር በከባድ መሣሪያዎች እና ቡልዶዘሮች የጸዳውን እና ወደ ምዕራባዊ ሜዲትራኒያን የባሕር ዳርቻ የሚወስደውን መንገድ ማየት እንችላለን።

ታንኮችን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከአፈር ከተሠሩ ምሽጎች ጀርባ ተሰባስበው ማየትም ይችላሉ።

የጋዛ ነዋሪዎች በፍርስራሾች መካከል መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመግዛት ወጥተው
የምስሉ መግለጫ,የጋዛ ነዋሪዎች በፍርስራሾች መካከል መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመግዛት ወጥተው

በጋዛ ከተማ በሚገኘው በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ በታንኮች ዱካ የተቀረጸ የዳዊት ኮከብ ያለበት ስፍራ መኖሩን የሳተላይት ምስሎቹ አክለው ያሳያሉ።

ከጦርነቱ በፊት በበይነ መረብ ላይ የነበሩ ምስሎች በቦታው ሕጻናት ሲጫወቱ ሲሳይ፣ መናፈሻ እንደነበርም ይጠቁማሉ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ግን ሐማስ ከጣቢያው አቅራቢያ የሚገኘውን ቦታ ወታደራዊ ሰልፍ ለማሳየት ይጠቀምበት ነበር ብለዋል። አካባቢው በእስራኤል ጦር ጎላኒ ብርጌድ ቁጥጥር ስር ወድቋል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተገደሉትን የእስራኤል ወታደሮች ለማሰብ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ የአይሁዶች እና የእስራኤል ምልክት ሆኖ የሚያገለግለው የዳዊት ኮከብ በወታደራዊ መኪኖች አማካይነት መሠራቱን ሃጋሪ በኤክስ ላይ አስፍረዋል።

ጋዛ