
ከ 5 ሰአት በፊት
በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ደም አፋሳሽ የእስር በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው የአክሱም ጽዮን ማሪያም ክብረ በዓል ላይ ለመታደም ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ወደ ስፍራው መጓዙን የአክሱም ከተማ ከንቲባ ተናገሩ።
የእግዚአብሔር የቃል ኩዳኑ ታቦት የሆነው የሙሴ ጽላት መቀመጫ እንደሆነች የምትታመነው የአክሱም ከተማ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ቅዱስ ስፍራ ናት።
አርብ ኅዳር 21/2016 ዓ.ም. በተከበረው ዓመታዊው የጽዮን ማሪያም ንግሥት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን እና ጎብኚዎች ከትግራይ፣ ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እና ከሌሎች አገራት ወደ አክሱም ተጉዘዋል።

ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ 200 ኪሎ ሜትሮች ያህል ተጉዛ በበዓሉ ላይ የታደመችው ማኅሌት ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፣ ወደ አክሱም ጽዮን በመሄድ በበዓሉ ላይ ለመታደም የሕይወት ዘመኗን ሙሉ ስትጠብቅ ቆይታለች።
ይህ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የሚገኝበት ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል፣ ከባድ ውድመትን አስከትሎ መቶ ሺዎችን በገደለው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳይካሄድ ቀርቷል።
የንግሥት ሳባ የትውልድ ስፍራ እንደሆነች የሚነገርላት ታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ በጦርነቱ ወቅት ከባድ ጉዳት ካጋጠማቸው የክልሉ አካባቢዎች መካከል አንዷ ናት።
በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉበት የሚነገረው ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባት የመብት ድርጅቶች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በአክሱም ጸዮን ማሪያም ዓመታዊ በዓል ላይ ለመገኘት ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ከአዲስ አበባ ተጉዛ አክሱም የደረሰቸው ምሕረት ገበረአናኒያ ከስፍራው መገኘቷ ደስታን ፈጥሮላታል።
በጦርነቱ ወቅት ትግራይ ውስጥ የሚኖሩት ቤተሰቦቿ ደኅንነት ያስጨንቃት እንደነበረ የምትናገረው ምሕረት፣ አሁን በክልሉ ያለው ሁኔታ በአንጻራዊነት ሰላም በመሆኑ ደስተኛ መሆኗን ለቢቢሲ ገልጻለቸ።

በዓመታዊው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙት ቀሳውስት በክልሉ ውስጥ ስለተፈጠረው ሰላም ለእግዚአብሔር ምስጋና አድርሰዋል።
በዓሉ ላይ ለመታደም ከመላው አገሪቱ የመጡት ምዕመናን በጦርነቱ ወቅት የተለያየ አቋም ይዘው የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ግን በአክሱም ጽዮን ማሪም ክብረ በዓል ላይ በሰላም ታደመዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የታደመበት ይህ በዓል በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን የተካሄደ ሲሆን፣ ቀሳወስት በጥንታዊው የአክሱም ሃውልት አጠገብ ካለው መስክ ላይ በመሆን ሥነ ሥርዓቱን አካሂደዋል።
የጥንታዊው አክሱም መንግሥት መቀመጫ በነበረችው ከተማ ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙ ሲሆን፣ የአክሱም ሃውልቶች ጎልተው የሚታዩት ናቸው።

ከተለያዩ አካባቢዎች የአክሱም ጽዮን ማሪያምን ዓመታዊ በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ለሦስት ዓመታት ሲጠባበቁ የነበሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የእንግዶችን እግር ከማጠብ ጀምሮ የሚበላ እና የሚጠጣ በማቀረብ ሲያስተናግዱ ነበር።
የበዓሉ ታዳሚዎች ከሆቴሎች ባሻገር በአክእሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ እና በከተማዋ ባሉ ነዋሪዎች ቤት ውስጥ ነው የቆዩት።
