Saturday, 02 December 2023 19:36

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ

የአሜሪካ ኤምባሲ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ሲል መጥራቱ ተቃውሞን አስነሳ

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያደረገው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ርዕሰ መዲናይቱን አዲስ አበባን ፊንፊኔ ሲል መጥራቱን ሃያሁለት  የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ተቃወሙት። ማህበራቱ ተቃውሞአቸውን በመግለፅ ለአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ቢሊንከን ደብዳቤ ልከዋል።
ኤምባሲው የሚሰጣቸውን የቪዛና ሌሎች አገልግሎቶችን አስመልክቶ ከትናት በስቲያ በማህራዊ ትስስር ገፁ ላይ በአፋን ኦሮሞ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ አዲስ አበባ በሚለው የርዕሰ መዲናይቱን መጠሪያ ምትክ “ፊንፊኔ” የሚለውን ስም ተጠቅሟል።  ይህን የኤምባሲውን አጠራር ተከትሎ ተቀውሞአቸውን ያሰሙት በአብዛኛው ነዋሪነታቸውን በውጪ አገር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሲቪክ ድርጅቶች ለአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ደብዳቤ ልከዋል።
 ማበራቱ በዚሁ የተቃውሞ ደብዳቤአቸው “በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪከ ኤምባሲ አጨቃጫቂ በሆነውና በአክራሪ የኦሮሞ ቡድኖች የሚቀነቀነውን “ፊንፊኔ” የሚለውን ስም በመጠቀሙ ቁጣችንን እንገልጻለን ብለዋል። በሌላ በኩል ይህን የኤምባሲውን አጠራር የደገፉ የኦሮሞ ማህረሰብ ድርጅቶች ኤምባሲው ርዕሰ መዲናዋን የጠራበት ፊንፊኔ የተሰኘውን መጠሪያ የሚደግፉ መሆኑን አመልክተዋል።