December 3, 2023 –

በምሥራቅ አርሲ ሮቤ  የኅዳር ጽዮንን በዓል አክብረው በተመለሱ ሦስት ኦርቶዶክስ ምዕመናን ላይ ግድያ መፈጸሙን ሀገረ ስብከቱ አስታወቀ።

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሮቤ ወረዳ ቤተ ክህነት  ወልተኢ  ቀበሌ ገበሬ ማኅበር በደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም  የኅዳር ጽዮንን በዓል አክብረው በሚመለሱ  ሦስት ምዕመናን ላይ  ግድያ መፈጸሙን ሀገረ ስብከቱ ለጣቢያችን መረጃውን አድርሶናል።

ግድያው የተፈጸመው  ትናንት ኅዳር 21/2016 ዓ/ም   ከክብረ በዓሉ ፍጻሜ በኋላ  ምሽት 12:00 ሰዓት አካባቢ መሆኑም ተገልጿል።
በግፍ ከተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን መካከል አባትና ልጅ የሚገኙበት ሲሆን  ስማቸውም
1.አቶ ቃኛው ይልማ
2.አቶ ሙላቱ ቱሉ
3.አቶ ጌቲ ሙላት (የአቶ ሙላቱ ልጅ) የሚባሉ ሲሆኑ በምሥራቅ አርሲ ዞን በሮቤ ወረዳ ወልተኢ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪዎች የነበሩ ናቸውም ተብሏል።

ሀገረ ስብከቱ  የመከራውን ግፍና ኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት እያሳወቀ ቢሆንም እስካሁን ግን ምንም  ሊሻሻል አለመቻሉንም ለጣቢያችን ጨምሮ  ገልጿል።

በቅርብ  ወራት ወስጥ በምሥርቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሥር   በዴራ አማኑኤል  የካህናት ግድያ ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ከ ኅዳር 14 እስከ 17/2016 ዓ/ም  በሦስት ቀናት ውስጥ  በተለያዩ ቀበሌዎች 36 ኦርቶዶክሳውያን የተገደሉ ሲሆን  ከነዚህም  ከአንድ ቤተሰብ ብቻ 8 ኦርቶዶክሳውያን በጅምላ መገደላቸው የሚታወስ ነው።