
ከ 6 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ጦር መርከብ ሶስት ድሮኖችን ቀይ ባሕር ላይ መትቶ መጣሉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ገልጿል።
ድሮኖቹ ሶስቱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲቃጡ ነው የአሜሪካ ጦር መከርብ እርምጃውን የወሰደው።
ከ14 ሃገራት ጋር ግንኙነት ያለው ዩኤስኤስ ካርኒ የተሰኘው የጦር መርከብ እሑድ ዕለት በኢራን ከሚደገፉት የየመን ሁቲ አማፂያን ጋር ሲዋጋ መዋሉ ተሰምቷል።
ማዕከላዊ ዕዙ እንደገለጠው ሁለት የንግድ መርከቦች በሚሳዔል ቢመቱም የተጎዳ ሰው ግን የለም።
የሁቲ አማፂያን ቃል አቀባይ ሁለት የእስራኤል መርከቦች ከቡድኑ ባሕር ኃይል ጥቃት እንደደረሰባቸው አሳውቀዋል።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች በአውሮፓውያኑ 2014 መንግሥት ተገልብጦ የእርስ በርስ ጦርነት ከተከሰተ ጀምሮ አንዳንድ የሃገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥረው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ቡድኑ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ከተቀሰቀሰው የእስራኤል ሐማስ ጦርነት በኋላ ቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ የእስራኤል መርከቦችን ዒላማ እያደረገ ይገኛል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጠው እሑድ ጥዋት ዩኤስኤስ ካርኒ ፀረ-መርከብ ባሌስቲክ ሚሳዔል ዩኒቲ ኤክስፕሎረር ወደተሰኘ የዩናይትድ ኪንግደም የንግድ መርከብ ተተኩሷል።
- በኪሲንጀር ትዕዛዝ ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ቦምብ የዘነበባት ካምቦዲያ እንዴት ታስታውሳቸዋለች?ከ 6 ሰአት በፊት
- “በውሻ መነከስ፣ ድብደባ እና ምግብ መከልከል” የፍልስጤማውያን መከራ በእስራኤል እስር ቤቶች3 ታህሳስ 2023
- ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ እስራኤል ከባድ የአየር ጥቃት መፈፀሟን ነዋሪዎች ተናገሩ3 ታህሳስ 2023
ከዚህ ጥቃት በኋላ ሌላ ድሮን ወደ ጦር መርከቡ ቢሰነዘርም ሊያከሽፍ መቻሉን ያሳወቀው ዕዙ ጥቃቱ የአሜሪካ ጦር መርከብን ዒላማ ስለማድረጉ ግን እርግጠኛ አይደለንም ብሏል።
በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት ዩኒቲ ኤክስፕሎረር ከሁቲ ቁጥጥር ሥር ከሚገኝ ሥፍራ በተተኮሰ ሚሳዔል ተመትቶ አነስተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
የአሜሪካ ጦር መርከብ ሌላ የድሮን ጥቃት እንደተሰነዘረ ከተገነዘበ በኋላ ጥቃቱ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መትቶ እንደጣለው ተነግሯል።
ከዚህ ጥቃት በኋላ ደግሞ ሁለት የፓናማ ባንዲራ የሰቀሉ መርከቦች በሚሳዔል ጥቃት እንደተመቱ ተዘግቧል። ዩኤስኤስ ካርኒ እኒህን መከርቦች ለመርዳት እየሄደ ሳለ ሌላ የድሮን ጥቃት ተሰንዝሮ እሱንም ማክሸፉን አሳውቋል።
ማዕከላዊው ዕዝ እንዳለው ጥቃቶቹ መርከቦቹ ላይ የሚሰሩ የበርካታ ሃገራት ዜጎችን “ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል” ይህ ደግሞ “ለዓለም አቀፍ ንግድና የባሕር ጉዞ ስጋት ነው።”
“አልፎም እኒህ ጥቃቶች የመን ከሚገኙ ሁቲዎች ይሰንዘሩ እንጂ በኢራን እየተደገፉ እንዳለ እናምናለን” ብሏል።
“ዩናይትድ ስቴትስ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በመሆን ተመጣጣኝ ምላሽ እንደምትሰጥ ልንገልጥ እንወዳለን።”
በያዝነው ሳምንት መባቻ አሜሪካ፤ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ መርከቦች ላይ ጥቃት ያደረሱ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ገልጣ ነበር።
ሁቲዎች ራሳቸውን በኢራን ከሚደገፉ ቡድኖች ጋር “የተቃውሞ ዘንግ” ብለው የሚጠሩ ሲሆን እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስና መላው የምዕራቡ ዓለምን የሚቃወሙ ናቸው።
