
ከ 5 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ስምምነት ለመፈረም ወደ ሩዋንዳ አቀኑ።
ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሩዋንዳ ሲያመሩ ሦስተኛው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው። እስካሁን ግን ወደ ሩዋንዳ የተመለሰ ስደተኛ የለም።
ቀደም ብሎ ሃሳቡን ያመነጩት ፕሪቲ ፓቴል እንዲሁም ሱዌላ ብሬቨርማን በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ወደ ሩዋንዳ ተጉዘው ነበር።
ፕሪቲ ፓቴል ዩኬ ሕገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ ያስቀመጠችውን እና ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ይረዳል የተባለውን እቅድ ለማስፈፀም ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር የተጓዙት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።
ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በላይ ቢቆጠርም እንዲሁም በርካታ ፖለቲከኞች ቢጓዙም፣ ፖሊሲው መሬት ላይ ሳይወርድ ቆይቷል።
የዩኬ መንግሥት የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ በመላክ ጉዳያቸውን ከዚያ ሆነው እንዲከታተሉ ማድረግ ይፈልጋል።
ሆኖም ይህ ፖሊሲ ባለፈው ወር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
ፍርድ ቤቱ ወደ ሩዋንዳ የሚላኩት ጥገኝነት ጠያቂዎች ተይዘው ወደ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ ይህም የዩኬንና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል በማለት ነበር ፖሊሲውን ውድቅ ያደረገው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ግን ሃሳቡን እንደሚገፉበት ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 ሚያዚያ ወር ላይ የተዋወቀው ስደተኞችን የተመለከተው የአምስት ዓመት እቅድ፣ የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ በመላክ እዚያው ባሉበት የጥገኝነት ማመልከቻቸውን እንዲያቀርቡ የሚያደርግ ነው።
በዚህ እቅድ መሠረትም ስደተኞቹ በሩዋንዳ ለመቆየት የስደተኛ መታወቂያ የሚሰጣቸው ሲሆን እና እዚያ መኖር አሊያም በሌላ ሦስተኛ አገር ጥገኝነት መጠየቅ ይችላሉ።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞች ከባለፈው ዓመት ጥር ወር በኋላ ወደ ሩዋንዳ ይላካሉ ብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም።
በአሁኑ ላይ የተያዘው እቅድ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውና በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ላይ ውጤት ለማስገኘት ያለመ ነው።
ይህም የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለማምለጥ የሚረዳና ሁሉንም ሃሳብ ለመተግበር የሚደረግ አዲስ ሙከራ ነው ተብሏል።
- ኤችአይቪን የሚከላከለው መድኃኒት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል? ለማንስ ነው የሚሰጠው?ከ 8 ሰአት በፊት
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአርሲ 36 ምዕመኖቿ መገደላቸውን አጥብቃ አወገዘችከ 5 ሰአት በፊት
- ለኢትዮጵያውያን፣ ለየመናውያን እና ለኤርትራውያን የሥራ ዕድል የፈጠረው ስደተኛከ 8 ሰአት በፊት
ጥረቱ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ሙከራዎች ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል።
ሆኖም ሩዋንዳ የምትቀበለው ስደተኞች ቁጥር ጥቂት ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ይህም ስደተኞችን የመላኩን ተስፋ ምን ያህል እንደሚያመነምን በእርግጠኝነት አይታወቅም።
ሚኒስትሮች ጥረት መደረጉን ጥሩ ነው ቢሉም፣ ሌበር ፓርቲ ደግሞ ጊዜ ማጥፋት ነው ብሎታል።
የሌበር ፓርቲ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን “ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ቀን ከተቆረጠና በመጨረሻው ሰዓት ከተዘረዘ በኋላ አንድ ዓመት ፣ ከአምስት ወር ፣ ከ20 ቀን፣ ከአንድ ሰዓት ገደማ ሆኖታል” ሲሉ ያለፈውን ጊዜ አስልተዋል።
“ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሌሎች 63 ሺህ 852 ስደተኞች በትንንሽ ጀልባዎች የእንግሊዝ ቻነልን አቋርጠዋል” ብለዋል ባለሥልጣኑ።
ሌበር ፓርቲ ምርጫውን ካሸነፈ ከሚረከባቸው ጉዳዮች አንዱም ይህ ይሆናል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት እቅዱን ለማስፈፀም ሁሉንም ነገር እንዳደረጉ ቢገልጹም፣ ሌበር ግን ከዚህ በላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።
አሁን ላይ የስምምነቱ ዝርዝር እየተጠበቀ ሲሆን ጀምስ ክሌቨርሊ ከሩዋንዳ ከተመለሱ በኋላ በደረሱበት ውል ላይ የታቀደውን አዲስ ሕግ ለታችኛው ምክር ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ጨርሶ የማባረር ሥልጣን ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰጠቱ ይታወሳል።
በዚህ እቅድ መሠረትም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስደተኞቹን ከአገር ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ፣ ከዚያ በኋላ ወደ ዩኬ እንዳይገቡ እግድ የመጣል ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ተቀናቃናቸው ሌበር ፓርቲ መሪ ግን ሕጉ “መናኛ እና የማይሰራ” ሲሉ ተችተውታል።
