
5 ታህሳስ 2023, 16:30 EAT
በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ወገል ጤና ከተማ አምቡላንስ ላይ በተፈፀመ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት አሽከርካሪው እና አንድ የሕክምና ባለሙያን ጨምሮ በአቅራቢያው የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አምቡላንሱ ከደሴ ከተማ መድኃኒት ጭኖ እየተመለሰ ሳለ ነበር ጥቃቱ የተፈፀመበት።
በዚህ ጥቃት አሽከርካሪው እና አንድ የመድኃኒት ባለሙያ (ፋርማሲስት) ሲገደሉ፣ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ አንስቶ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተፈጸሙ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ከጥቃቱ በሕይወት የተረፉት የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ጌታቸው እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ባለቤታቸው ወ/ሮ እፀገነት አዳሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ግራ እጁ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፤ በጭስ የመታፈን አደጋ እንዲሁም የማስታወስ ችግር ገጥሞታል፤ ነገር ግን ለክፉ የሚሰጠው አይደለም” ሲሉ ባለቤታቸው ስለሚገኙበት ሁኔታ አስረድተዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 20/2016 ዓ.ም ከሰዓት 11፡00 ሰዓት ገደማ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት፣ በአቅራቢያው በግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የቀን ሠራተኞች እና የቤቱ ባለቤትም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በጥቃቱ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲገደሉ 3 ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ነዋሪው “አምቡላንሱ መድኃኒት ነበር የጫነው። ከጥቃቱ በኋላ ወደ ስፍራው ስንሄድ እየጨሰ ተመልክተናል” ሲሉም መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ እየተጎዳ ያለው ሰላማዊ ነዋሪው እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደ አዲስ ለማዋቀር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሠራዊት ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
ከሳምንታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫም በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት እየተፈፀሙ ያሉት የድሮን ጥቃቶች እና ሌሎች ግጭቶች እንዳሳሰበው መግለጹ ይታወሳል።
- በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ18 ህዳር 2023
- በአማራ ክልል ግድያ እና መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡ ኢሰመኮ30 ጥቅምት 2023
- በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ18 ህዳር 2023
በአምቡላንሱ ላይ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ሰፊ የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ እንዳለ የገለጹት አንድ ነዋሪ፣ የመንግሥት ተቋማት ዝግ መሆናቸውን እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አካባቢው ዋነኛ የጦርነት ቀጠና የነበረ ሲሆን፣ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት መዘገቡ ይታወሳል።
በወቅቱ በዘረፋ እና ውድመት ንብረታቸውን እንዳጡ ያስታወሱት ነዋሪው፣ ቦታው ከቀደመው ጦርነት ጉዳት ሳያገግም “ድጋሚ የጦርነት ቀጠና መሆኑ ሕይወታችንን ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል።
“በከተማው ውስጥ መከላከያም ሆነ ፋኖ ቢገባም የተረጋጋ አስተዳዳር የለም” የሚሉት ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ፣ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታ የዋጋ ንረት እና በመድኃኒት እጦት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ግንቦት ወር ላይ መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት እና እንደገና የማዋቀር እርምጃ ከጀመረ በኋላ ነበር በአካባቢው አለመረጋጋት የተፈጠረው።
“አንዴ ፋኖ ሲገባ፣ ሌላ ጊዜ መከላከያ አካባቢውን ሲቆጣጠር ነው የቆየው” የሚሉት ነዋሪ፣ ከአንድ ወር ገደማ ወዲህ ግን አካባቢው በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“መከላከያ ሲወጣ የመንግሥት ኃላፊዎች ወጥተው ይሄዳሉ። አገልግሎት አይሰጡም። ትምህርት ቤቶች አልፎ አልፎ ክፍት ቢሆኑም አሞራ ሲያንዣብብ ተማሪዎች በስጋት ይበተናሉ” ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አሁን ላይ በአካባቢው ወጊያ ባይኖርም የስጋት ኑሮ እየገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግጭቱ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ ወደዚያ የሚያደርሱ መንገዶች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም።
መንግሥት እስካሁን ተፈፀሙ ለተባሉት ጥቃቶች ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ ከክልል እና ከፌደራል ባለሥልጣናትናት ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ሙከራዎች አልተሳኩም።
