December 5, 2023 – Konjit Sitotaw 

“በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በጎርፍና በተፈጥሮ አደጋ ከ 6 መቶ ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል” ኦቻ

በኢትዮጵያ በጥቅምት እና ህዳር ወር ውስጥ ባለው ጊዜ በደረሱ የጎርፍና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ 1.5 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ተጠቂ መሆኑን የተመድ የሠብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በሪፖርቱ ጠቅሷል።

በተለይም የሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልሎች ከፍተኛ ጉዳት አስተናግደዋል ተብሏል። በአጠቃላይ እስከ ህዳር 17 ባለው ጊዜ 632,700 ሰዎች መፈናቀላቸውየተገለጸ ሲሆን 57 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

በሶማሊ ክልል ብቻ በደረሰው አደጋ በዚህ አደጋ የተፈናቃዮች ቁጥር 500,000 እንጀሚሆንና 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በአደጋው ጉዳት እንደደረሰባቸው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከሴቭ ዘ ችልድረን ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል እስካሁን ድጋፍ ያገኙት #10 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the children) የሱማሌ ክልል ቅርንጫፍ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ በዚህ የተፈጥሮ አደጋ የተጎዳ ሲሆን፥ የ 10 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ከ3 መቶ ሺ በላይ ሰዎች ተጎድተዋል፤ ከ84 ሺ ሄክታር በላይ ላይ የተዘራ እህል ወድሟል፤ 317 በላይ እንስሳት ሞተዋል እንዲሁም ከ18 ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ሲል ኦቻ ገልጿል።

ሌላው በዚህ የተፈጥሮ አደጋ የተጎዳው አከባቢ የዳሰነች ወረዳ ሲሆን በወረዳዋ ካሉ 40 ቀበሌዎች ውስጥ 27ቱ በውኃ ሙላት መዋጣቸው ተነግሯል።

በዚሁ ምክንያት በርካታ የቤት እንስሳት ወደ ኬንያ እና አዋሳኝ ወደሆኑት ሐመር እና ኛንጋቶም ወረዳዎች ተሰደዋል።

እንደ ኦቻ ሪፖርት በግምት 889,454 የቤት እንስሳት (534,320 ከብት፣ 180,750 ፍየል፣ 174,384 በጎች) ተሰደዋል። 2.99 ሚሊዮኑ  የቤት እንስሳት ደግም በውሃ ተከበዋል ብሏል።

በእነዚህ አከባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማድረስ ጥረቶች እንዳሉ አቻ በሪፖርቱ ጠቅሷል።