
ከ 2 ሰአት በፊት
ሐማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት በርካቶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከመስረም 26ቱ ጥቃት በኋላ ጥቃቱ ከተፈጸመበት አካባቢ የሰዎችን አስክሬን እና ተጎጂዎችን ያነሱ እማኞች በተጎጂዎች አካል ላይ ፆታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መልክቶች መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ተጎጂዎቹ ከሕጻናት እና ታዳጊ ሴቶች እስከ ጡረተኛ አዛውንት እናቶች ይገኙበታል ተብሏል።
ተጎጂዎቹ በሐማስ ተዋጊዎች በቡድን የተደፈሩ ሲሆን፤ ተጎጂዎችን ከጥቃቱ ስፍራ ያነሱ ሰዎች የተቆራረጠ የሰውነት ክፍል፣ ቁስል እንዲሁም ዳሌ እስከመሰበር ከፍተኛ የጉዳት ምልክት የጥቃቱ ሰላባ በሆኑ ሴቶች ላይ መመልከታቸውን አስታውቀዋል።
ፖሊስ የጥቃቱን ደረጃ ያሳያል ያለውን የአንዲት ሴት ምስክርነትን በተንቀሳቃሽ ምስል ለጋዜጠኞች አሳይቷል።
በቪዲዮ ላይ ምስክርነት የምትሰጠዋ ሴት የሐማስ ተዋጊዎች አንዲት ሴትን በቡድን ሆነው ሲደፍሩ እና አካሏን በስለት ሲቆራርጡ መመልከቷን ትናገራለች።
የዐይን እማኟ ተዋጊዎቹ የሴቷን ጡት በስለት ከቆረጡ በኋላ መንገድ ላይ መጣላቸውንም እንዲሁም ሴቶችን መድፈር እና በጥይት ጭንቅላቷን ተመትታ የተገደለች ሴት ማየቷን ገልጻለች።
- እስራኤል የሐማስን ዋሻዎች ከባሕር በሚሳብ ውሃ በማጥለቅለቅ ልታወድም ነውከ 6 ሰአት በፊት
- ቀይ መስቀል ታጋቾችን በማስለቀቁ ሂደት ምን ሚና ነበረው?ከ 6 ሰአት በፊት
- ሳምንታትን በፍርሃት፣ በእንግልት እና በረሃብ ያሳለፉት የሐማስ ታጋቾች ታሪክ29 ህዳር 2023

ኖቫ ፌስቲቫል በተባለው ስፍራ ተሳታፊ የነበረ የዐይን እማኝ ለቢቢሲ ሲናገር ሰዎች ሲገደሉ፣ ተገደው ሲደፈሩ እና አካላቸው በስለት ሲቆራረጥ የሚያወጡትን የሲቃ ድምጽ ስሰማ ነበር ብሏል።
“አንዳንዶቹ ሴቶች ቆስለው ሳለ ነው የተደፈሩት። አንዳንዶቹ ደግሞ ከተገደሉ በኋላ ነው በድናቸው በአሸባሪዎቹ የተደፈረው” በማለት ተናግሯል።
ሐማስ ተዋጊዎቹ ፆታዊ ጥቃት ፈጽመዋል መባሉን ከዚህ በፊት ሲያስተባብል ነበር።
በሐማዝ የተቀረጹ ጥቃቱን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ከወገባቸው በታች እርቃናቸውን ሆነው የወደቁ የሴቶች ምስልን አሳይቷል።
የእስራኤል የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ማያ ጎላን በሐማስ ታጣቂዎች ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው በሕይወት የተረፉ ሴቶች መኖራቸውን ተናግረው፣ የሥነ አእምሮ ጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ኃላፊ ያኮቭ ሻባታይ በተመሳሳይ ከጥቃቱ የተፉ በርካቶች ስለክስተቱ ማሰብ እጅግ ስለሚከብዳቸው ስለደረሰባቸው ማውራት አይፈልጉም ብለዋል።
“አብዛኞቹ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ተገድለዋል። በጣም ጥቂቶች ግን በሕይወት ተርፈዋል” ያሉ ሲሆን፣ አሁን ላይ 18 ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ወደ አእምሮ ጤና ሆስፒታሎች እንዲገቡ መደረጋቸውን እና ለመንግሥት ኃይልም ሆነ ለሚዲያ አካላት ስለሆነው ነገር መናገር አይችሉም በማለት ያሉበትን ሁኔታ ተናግረዋል።
በሂብሩ ዩኒቨርስቲ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኮቫቭ ኤልካያም-ሌቪ ሐማስ ፆታዊ ጥቃትን እንዴት እንደ ጦር መሳሪያ አድርጎ መጠቀም እንደሚቻል ከኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ተምሯል ይላሉ።
የሐማስ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት የሚመረምረው የፖሊስ ኃይል አባል የሆኑት ዴቪድ ካትዝ በጥቃቱ ፆታዊ ጥቃት መፈጸም ቀድሞም የሐማስ ዕቅድ አካል መሆኑን ማስረጃዎች ያሳያሉ ይላሉ።
የፖሊስ አባሉ እንደሚሉት ከሐማስ ተዋጊዎች የእጅ ስልክ የተገኙ መረጃዎች ፆታዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ ለመጠቀም “ቀድሞ በዝርዝር ዝግጅት እንደተደረገበት” ያመለክታሉ ብለዋል።
