የፖሊስ ተሽከርካሪ

ከ 4 ሰአት በፊት

በቀጣዩ የበዓላት ወቅት በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ “ከባድ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለቸው አንድ የኅብረቱ ባለስልጣን ገለጹ።

የአውሮፓ ኅብረት የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽን ኃላፊ ይልቫ ጆሃንሰን በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ምክንያት በማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው መካረር የጥቃቶችን ስጋት እንደጨመረው ተናግረዋል።

በዚህም ስጋት ምክንያት ኅብረቱ ለተጨማሪ የደኅንነት ጥበቃ 30 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ጁሃንስን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ ይህንን ከማለታቸው ከቀናት አስቀድሞ ፓሪስ ውስጥ አንድ ጎብኚ በስለት ተወግቶ ተገድሎ ነበር።

ሆኖም ባለስልጣኗ በፈረንጆቹ የገና እና አዲስ ዓመት በዓላት ወቅት የሽብር ጥቃት አለ ለማለት ያስደፈራቸው የተለየ መረጃ ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም።

ጆሃንሰን ከአውሮፓ ኅብርት የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሮች ስብሰባ በፊት በሰጡት አስተያየት “ይህንን ጉዳይ በቅርቡ ፓሪስ ውስጥ አይተነዋል። እንዳለመታደል ሆኖ ከዚያ ቀደምም ተመልክተነዋል” ብለዋል።

በተመሳሳይ የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም “ጽንፈኝነትና ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች” በበረከቱበት ጊዜ የአውሮፓ ኅብረት የቅርብ ክትትል ሊያደርግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የእስራኤልና ሐማስ ግጭት ከሁለት ወራት በፊት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአውሮፓ አገራት ጥላቻን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎች ተበራክተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ፓሪስ ውስጥ የ23 ዓመቱ ጀርመናዊ ቱሪስት በስለት ጥቃት ተፈጽሞበት ከተገደለ እንዲሁም ፍቅረኛውና ሌላ የብሪታኒያ ቱሪስት ጉዳት ከደረሰባቸው አንድ ቀን በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ለምክክር ተቀምጧል።

ሁለቱ ጀርመናውያን ጥንዶች ኤፍል ታውር (የፓሪስ ዝነኛ ማማ)ን ጨምሮ በፈረንሳይ የተለያዩ መስህቦችን እየጎበኙ ፎቶ ሲነሱ ነበር።

ጥንዶቹ ላይ ጥቃት እንደፈጸመው የተጠረጠረው የ26 ዓመት ግለሰብ ፈረንሳዊ ሃይማኖት አልባ ከሆነ ኢራናውያን ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን ለአይ ኤስ አጋርነቱን የገለጸ ነው።

ግድያው በተፈጸመበት ስፍራ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ከፓሪስ ወጣ ባለ አከባቢ የሸብር ጥቃት ለመፈጸም ሲያሴር ነበር በሚል ታስሯል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ደግሞ መምህር ከገደለ አንድ ግለሰብ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ተጠርጥሮ ለፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

የፈረንሳይ ጸረ ሽብር ዐቃቤ ሕግ የተጠርጣሪውን ባህሪ በተመለከተ እናቱ ስጋት እንዳላት ገልጻለች።

ባለፈው ሳምንት በገና ገበያ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ሲያሴሩ እንደነበር የተጠረጠሩና በተለያዩ ቦታ የነበሩ ሁለት ሰዎች ተይዘዋል።

በተመሳሳይ በገና በዓል ገበያ ላይ በስለት ጥቃት ሊፈጽም ነበር የተባለ ባለፈው ዓመት ጀርመን የገባ የ20 ዓመት ኢራቃዊ ወጣትም ታስሯል።

የጀርመን የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ከገና በዓል ባሻገር በቀጣይ በሚካሄዱ እንደ ፓሪስ ኦሊምፒክ እና አውሮፓ ሻምፒዮንሺፕ ያሉ ታላላቅ ሁነቶች ላይ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።