ቀይ መስቀል ከጋዛ ታጋቾች ጋር

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት ሐማስ እና እስራኤል ያደረጉትን የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥ ተከትሎ ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የንግግሮች ማዕከል ሆኖ ነበር።

ሐማስ የወሰዳቸውን ታጋቾችን በሚለቅበትም ወቅት ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ነው የተረከባቸው።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አርማ ያለበትን እጅጌ ጉርድ ጃኬት ያደረጉ ሠራተኞች ጭንብል ካጠለቁ ታጣቂዎች ታጋቾን ሲቀበሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም ወጥቷል።

ታጋቾችም ፈገግ ብለው ታጣቂዎቹን ተሰናብተው በቀይ መስቀል ሠራተኞች ታጅበው ወደ መኪኖች ሲገቡ ይታያሉ። መኪና ውስጥ ከገቡም በኋላ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ሲሰጧቸው እንዲም ከሕጻናቱም ጋር ሲጫወቱ ከቪዲዮዎቹ መመልከት ይቻላል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በእስራኤል ጥቃት ፈጽሞ 240 የሚሆኑ ታጋቾችን ከወሰደ በኋላ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ሐማስን በማናገር ላይ ይገኛል። ማኅበሩ በተደጋጋሚ እንዲለቀቁ ጥሪ ከማቅረብ በተጨማሪም ቢያንስ ታጋቾቹን ለመጎብኘትም ጥሪ አቅርቧል።

በሐማስ እና በእስራኤል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ከ100 በላይ እስራኤላውያን እና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ታጋቾች ለቀይ መስቀል ተሰጥተው ተለቀዋል።

ተቋሙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በተደረገው ድርድር ተሳታፊ ባይሆንም፣ ታጋቾችን በመረከብ እንዲሁም በማጀብ ተሳታፊ ሆኗል።

 በሁቲ ተይዘው የነበሩ እስረኞችን ቀይ መስቀል ሲያጓጉዝ
የምስሉ መግለጫ,በሁቲ ተይዘው የነበሩ እስረኞችን ቀይ መስቀል ሲያጓጉዝ

እስራኤል ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ከዚህ በላይ ማድረግ ይገባው ነበር በማለት ስትተች ይደመጣል።

እስራኤል የምታወጣቸው መግለጫዎች ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ምን ማከናወን ይችላል? ምንስ ማድረግ አይችልም? የሚለውን ካለመረዳት የመጣ ብስጭት ነው።

በጄኔቫ ኮንቬንሽን መሠረት ቀይ መስቀል ያለው ሚና ታጋቾችን ለመጎብኘት መጠየቅ፣ አስፈላጊ መድኃኒቶች እና ግብዓቶችን ለታጋቾች ማድረስ እንዲሁም ለታገቱ ቤተሰቦች ዜናውን ማድረስ ይገኙበታል።

ሆኖም በጋዛ ታጋቾች ጉዳይ ቀይ መስቀል እነዚህን ተግባራት ማከናወን ይችል የነበረው ሐማስ እና እስራኤል ስምምነት ላይ ቢደርሱ ነበር።

ቀይ መስቀል ትጥቅ የለውም። በጦርነት አካባቢዎችም ተግባሩን ማከናወን ይችል ዘንድ በተፋላሚ ኃይሎች ውጊያ የማቆም ስምምነት ላይ የተመሠረተ ነው።

በጋዛ የነበሩ ታጋቾችን እንዳጓጓዘው በልውውጡ የተፈቱ በእስራኤል እስር ቤቶች የነበሩ ሕጻናት እና ፍልስጤማውያን ታሳሪዎች ወደየቤታቸው ዌስት ባንክም አጓጉዟል።

ታጋቾችን እና እስረኞችን ለማጓጓዝ የሚያስፈልገው ሎጂስቲክስ የተወሳሰበ ነው። ለቀይ መስቀል በተወሳሰቡ ሂደቶች ማለፍ አዲስ ነገር አይደለም።

ባለፈው ዓመት በየመን ውስጥ በኢራን መንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የያዟቸውን 900 እስረኞችን እንዲለቀቁም በማመቻቸቱም ረገድ ተቋሙ ሚና ተጫውቷል።

ቀይ መስቀል ይህንን ዘመቻ ለማከናወን ሁለት ቀናት ፈጅቶበታል። ሁሉንም ታሳሪዎች መጎብኘት፣ ለመጓዝ ይችላሉ የሚለውን የጤና ሁኔታ መገምገገም እንዲሁም በጦርነት ቀጠና የሚበሩ አውሮፕላኖችንም መከራየት ነበረበት።

በወቅቱም የቀይ መስቀል የመካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር የነበሩት ፋብሪዝዮ ካርቦኒ እስረኞቹን የማጓጓዝ ሂደት በሰላም በመከናወኑ የተሰማቸውንም እፎይታ ገልጸዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ይላሉ ዳይሬክተሩ “የእርዳታ ሠራተኛ ሕይወት በብስጭት የተሞላ ነው። እባካችሁ የበለጠ ቁጥር ስጡን፣ አዎ፣ አይሆንም” ይበዙበታል ይላሉ።

የቀይ መስቀል ሰራተኞች በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እገዛ ሲያደርጉ
የምስሉ መግለጫ,የቀይ መስቀል ሰራተኞች በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እገዛ ሲያደርጉ

አዳዲስ ተግዳሮቶች

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የጋዛ ታጋቾችን ለመረከብ ያደረገው ዝግጅት አዲስ አይደለም፤ የረዥም የታሪኩ አካል እንጂ።

በጄኔቫ የሚገኘው የቀይ መስቀል ሙዚየም ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ የምዝገባ ካርዶችን ማኅደር ይዟል። የምዝገባ ካርዶቹ በሁለቱ ዓለም ጦርነቶች የጠፉ ግለሰቦችን ጨምሮ በርካታ የእስረኞችን ስም እና ዝርዝር ሁኔታዎችን የያዙ ናቸው።

ማኅደሩ የያዘው ስብስብ በጣም አስደናቂ ነው። በአንደኛው ካርድ ላይ በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወቅት የፈረንሳዩን ጦር የመሩት በኋላም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት ቻርለስ ደ ጎልን ስምን ይዟል።

ደ ጎል በአውሮፓውያኑ 1916 በነበረው የቬርዱን ጦርነት የጦር ምርኮኛ ሆነው መወሰዳቸውንም ያሳያል። በጦርነቶች ወቅት ደብዛቸው የጠፉ ልጆቻቸውን ለማግኘት ይሞክሩ የነበሩ እናቶች ምልጃ እና መከራ እንዲሁም መገደላቸውን የሚያሳይ ልብ የሚሰብሩ ምላሾችም ተካትተውበታል።

የማኅደሩ ስብስቦችም ቀይ መስቀል በጄኔቫ የተሰጡትን ቁልፍ የሆኑ ሚናዎችም ጉልት አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የጠፉ ሰዎችን መከታተል፣ ጠፍተው የሞቱ ሰዎችን አሟሟትም ማጣራት፣ የጦር እስረኞቸን መጎብኘት እና ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም በጦር እስረኞች እና ቤተሰቦቻቸው መካከል ያሉ የመልዕክት ልውውጦችን ማመላለስ ይገኙበታል።

ቀይ መስቀል በጀኔቫ ማዕከሉ በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት የጠፉ ቤተሰቦችን ማፈላለግ እንዲሁም የጦር እስረኞች እና ቤተሰቦቻቸውን በመልዕክት ማገናኘት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

ነገር ግን በአንደኛው የዓለም ጦርነት እና ከክፍለ ዘመናት በኋላ ያለው የቀይ መስቀል ሚና ሰፍቷል።

ጦርነቶች መልካቸውን ቀይረዋል። ባህላዊ ጦርነቶች በታጠቁ ሚሊሻዎች ተተክተዋል። ሰላማዊ ዜጎችም ሆኑ ተዋጊዎች ይወሰዳሉ እንዲሁም ይታሰራሉ፤ ይታገታሉ እንዲሁም ይጠፋሉ።

ሚናው ቢሰፋም የቀይ መስቀል ዓላማ አንድ ነው። የጠፉ ቤተሰቦች እና ዘመዶችን ዜና ማምጣት እናም ከተቻለ በጦርነት የተለያዩ ቤተሰቦችን ማገናኘት ነው።

በየመን በተደረገው የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት የተለቀቀ ግለሰብ ቤተሰቦቹን ባገኘበት ወቅት

ዓለም አቀፍ ትኩረት ያገኙ ክስተቶች

ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በጨቋኙ አፓርታይድ አገዛዝ ዘመን በሮቢን ደሴት እስር ቤት በነበሩበት ወቅት ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በተደጋጋሚ ጎብኝቷቸዋል።

ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት የቋጨው እና በዩናይትድ ኪንግደም እና በሰሜን አየርላንድ የሰላም እና የሥልጣን ክፍፍልን ያካተተው የጉድ ፍራይዴይ ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በሰሜን አየርላንድ ታስረው የነበሩ የልዩ ኃይል አባላትንም ቀይ መስቀል ይጎበኛቸው ነበር።

ቀይ መስቀል በተጨማሪም በእስረኞች ልውውጥ እንዲሁም የታገቱ እና በታጋችነት የተወሰዱ ሰዎችንም ለማስለቀቅም እርዳታ ያደርጋል።

በናይጀሪያ ቦኮ ሃራም በአውሮፓውያኑ 2014 በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ሴት ተማሪዎችን አግቶ በወሰደበትም ወቅት የተወሰኑትንም ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲለቀቁ ቀይ መስቀል የራሱን ሚና ተጫውቷል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የጋዛ ታጋቾች መለቀቅ ጋር ተያይዞ ማመቻቸት እንዲሁም ድጋፍ መስጠት እንጂ ተደራዳሪ አልነበረም።

“እንዲለቀቁ በተደረገው ድርድር ላይ አልተሳተፍንም። ከሁለቱም ወገኖች የተለቀቁ ታዳጊዎችን አስተላልፈናል” ሲልም ቀይ መስቀል በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በቅርቡ ከአለቃቸው ሚርጃና ስፖልጃሪች ጋር ሐማስና እስራኤልን ወዳሸማገለችው ኳታር አምርተው የነበሩት ፋብሪዝዮ ካርቦኒ፣ ቀይ መስቀል መሠረታዊ ሚናውን ሲመለከት በመቶ ዓመታት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንደሌለው አብራርተዋል።

“ልጆቼን እመለከታለሁ ከዚያም ወደ ወንድሞቼ አማትራለሁ። ጦርነት ተከስቶ ቢወሰዱ ብዬ አስባለሁ። እናም ማየት አልችልም። ይባሰ ብሎ ያሉበትን ሁኔታም ለማወቅ ምንም ዜና የሌለበትም ሁኔታ ይኖራል። ምን ታደርጋላችሁ። አይታወቅም” ይላሉ።

ለዚያም ነው ቀይ መስቀል እያከናወነ ያለው ተግባር ታላቅ ነው የሚሉት።

“ስለዚህ ሰዎችን እንደገና ለማገናኘት ስንሞክር እያደረግን ያለው ተግባር በቃላት ከመግለጽ በላይ እንደሆነ እንረዳለን” ይላሉ።