
ማኅበራዊ የትግራይ ክልል በወባና በኮሌራ 23 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስታወቀ
ቀን: December 6, 2023
በትግራይ ክልል በ50 ወረዳዎች በስፋት በተከሰተው ወባና ኮሌራ የ23 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በወባ ከ250 ሺሕ በላይ ሰዎች መጠቃታቸውንና ለክልሉ ጤና ቢሮ የቀረበው ሪፖርት የ17 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚያሳይ እንደሆነ፣ የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መቆጣጠር ቡድን መሪ አቶ መብርሃቶም ሀፍተ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በክልሉ በተከሰተው ወባ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳለ ገልጸው፣ በክልሉ አሥር ወረዳዎች በተከሰተው ኮሌራ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የቡድን መሪው አስረድተዋል፡፡
ኮሌራ የተከሰተው በራያ፣ በአላማጣና ገርጀሌ በሚባል ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ የፀበል ሥፍራ መሆኑን የተናገሩት የቡድን መሪው፣ እዚህ አካባቢ ደርሰው በተመለሱ ሰዎች ምክንያት መስፋፋቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ኮሌራ የተከሰተው ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑን፣ በሽታው በስፋት በመሠራጨቱ ከ100 በላይ ሰዎች ማጥቃቱንና ከእነዚህ ውስጥም የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አቶ መብርሃቶም አብራርተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በማይደርስባቸው ኮረምና ኦፍላ በሚባሉ ወረዳዎች ኮሌራ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን፣ የሕክምና አገልግሎትም ተደራሽ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ወባ የሚያዙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ችግሩንም ለመቆጣጠር ከክልሉ ጤና ቢሮ አቅም በላይ ነው ብለዋል፡፡
ወባን ለመቆጣጠር የጤና ቢሮው ለ20 ወረዳዎች የሚሆን አጎበር እንዲሰጠው ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን፣ ነገር ግን ለአሥር ወረዳዎች ብቻ ማግኘቱንና ይህም 46 በመቶ ለሚሆኑ ሰዎች ተደራሽ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በከፍተኛ መጠን የመድኃኒት ግብዓት እጥረት እንዳለበት የተናገሩት ቡድን መሪው፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ከወባና ከኮሌራ በተጨማሪ ሌሎች ሕመሞች መከሰታቸውን ገልጸው፣ ‹‹በክልሉ ባለው ድርቅና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ ድጋፉ በቂ እንዳልሆነና ለጉዳዩም አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
‹‹በተለይ በክልሉ ገጠራማ ቦታዎች የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ዝቅተኛ ነው፤›› ያሉት አቶ መብርሃቶም፣ ‹‹ይህንንም በመረዳት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ወባ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች ተከስቶ ብዛት ያላቸው ሰዎች መሞታቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
