ኪይቫ በዩክሬን ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ነበር

ከ 5 ሰአት በፊት

የቀድሞ የዩክሬን የፓርላማ አባል ኢሊያ ኪይቫ ኤስቢዩ በተባለው በዩክሬን የደህንነት አገልግሎት ሩሲያ ውስጥ መገደሉን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ወንጀለኛው የተገደለው ቀላል መሳሪያ በመጠቀም ነው” ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።

አስከሬኑ ከዋና ከተማዋ ሞስኮ ውጭ መገኘቱን የሩሲያ መርማሪዎች ገልጸዋል።

ኪይቫ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በከፍተኛ የአገር ክህደት እና ዩክሬን እንድትወረር በይፋ በመደገፍ ወንጀል የ14 ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

ቀደም ብሎ ከዩክሬን በመሸሹ ውሳኔው የተላለፈበት በሌለበት ነው።

በርካታ የዩክሬን መገናኛ ብዙሃንም ምንጮቻቸውን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከቀድሞው የፓርላማ አባል ግድያ ጀርባ ኤስቢዩ አለበት።

የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ቃል አቀባይ አንድሪ ዩሶቭ “ኪቫ በህይወት አለመኖሩን ማረጋገጥ እንችላለን። ይህ ዕጣ ፈንታ ሌሎች ዩክሬንን ለከዱ እና የፑቲን አገዛዝ አሻንጉሊት ለሆኑትም ይተርፋል” ሲሉ ለዩክሬን ቲቪ ተናግረዋል።

የሩሲያ ኤስኬ ግዛት መርማሪ ኮሚቴ ኪይቫ ከሞስኮ በስተ ምዕራብ በምትገኘው በሱፖኔቮ መንደር በጥይት ተመትቶ መሞቱን ቅድመ ምርመራዎች ያመለክታሉ ብሏል። የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቋል።

ኪይቫ እአአ በ2019 ለዩክሬን ፕሬዝዳንትነት ቢወዳደርም አልተሳካለትም። ሩሲያ ወረራ ከመፈጸሟ ከአንድ ወር በፊት ነበር አገሪቱን ለቆ የወጣው።

በሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚተላለፉ የፕሮፓጋንዳ ፕሮግራሞች ላይ መደበኛነት ተሳታፊ ነበር።

በሩሲያ የፖለቲካ ጥገኝነት ለመጠየቅ አቅዶ እንደነበርም ተዘግቧል።

በሌላ መረጃ ደግሞ በሩሲያ የሚደገፈው ፖለቲከኛው ኦሌግ ፖፖቭ ረቡዕ ዕለት በዩክሬን ምሥራቃዊ ሉሃንስክ ከተማ በመኪና ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት መሞቱን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

አብዛኛው የሉሃንስክ ግዛት በሩሲያ ቁጥጥር ስር ውሏል። ዩክሬን ስለጥቃቱ የተናገረችው ነገር የለም።

የሉሃንስክ ክልል የህግ አውጪ ሚካሂል ፊሊፖኔንኮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ ጥቃት ሲገደል ኪዬቭ ኃላፊነቱን ወስዳለች።

ከሩሲያ ወረራ ወዲህ ኤስቢዩ እና ወታደራዊ ደህንቱ በሞስኮ ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች እና በሩሲያ ከፍተኛ ስም ያላቸው ግለሰቦች ላይ ስኬታማ እርምጃዎችን ወስደዋል ።

ክሬሚያን ከሩሲያ ጋር የሚያገናኘው የሩሲያ ድልድይ ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶበት ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

ኤስቢዩ ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ከቻይና ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ ዋና የመጓጓዣ መስመር ሆኖ የሚያገለግለውን የባቡር ሐዲድ ማጥቃቱን ገልጿል።