ምግብ የያዘች አስተናጋጅ

6 ታህሳስ 2023

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተጋጆቻቸውን “የተራቆተ” ልብስ የሚያስለብሱ ከሆነ ከ50 ሺህ ብር እስከ እገዳ የሚደርስ ቅጣት የሚጥል ረቂቅ ተዘጋጀ።

በከተማዋ የባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ ደንብ አስተናጋጆች በሚታይ የሰውነት አካል ላይ ንቅሳት እንዳይኖራቸው እንዲሁም ወንዶች ጆሮ ጌጥ አድርገው እንዳያስተናግዱ እንደሚከለክልም ተገልጿል።

በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣ ጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ደንብ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ረቂቅ የተዘጋጀው በተለይ እንደ ሥጋ ቤቶች ባሉ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ በታየው የአስተናጋጆች “የተራቆተ አለባበስ” ምክንያት መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሃፍተይ ገብረ እግዚአብሔር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሴት አስተናጋጆች እንዲለብሱ የሚገደዱት የአጭር ቀሚስ ጉዳይ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር አካባቢ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ “ሠራተኞቻቸው ከመስተንግዶ ሥነ-ምግባር እና ከአገር ባህል የወጣ አለባበስ እንዲለብሱ በሚያደርጉ እና በሚያስገድዱ” አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ በማስጠንቀቅ ደብዳቤ ጽፎ ነበር።

ቢሮው ይህንን ማስጠንቀቂያ ቢያወጣም በጉዳዩ ላይ “ለውጥ ሊመጣ እንዳልቻለ” ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል። “የተጻፈው ደብዳቤ ‘ከዚህ ድርጊታችሁ ተቆጠቡ” የሚል እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሃፍተይ፤ “ማስጠንቀቂያው ከወጣ በኋላ ማስጠንቀቂያውን ተላልፈው ቢገኙ ‘በምን እንቀጣቸዋለን?’ የሚለውን ስንፈትሽ ግን [የምንቀጣበት ሕግ] አልነበረውም፤ ክፍተት አለበት” ሲሉ አሁን ለተዘጋጀው ደንብ ምክንያት የሆነው ጉዳይ አስረድተዋል።

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንደሚገልጹት አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን “አለባበስ፣ በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ የሚደረጉ የጌጣ ጌጦች አጠቃቀምን፣ የፀጉር አያያዝን እንዲሁም የሚጠቀሟቸው ሽቶዎች መጠንን” የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል።

ረቂቅ ደንቡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች “ከባህል፣ ከጨዋነት ያፈነገጠ እና የተራቆተ” አለባበስ እንዳይኖራቸው እንደሚከለክል የጠቆሙት አቶ ሃፍታይ፤ ሌሎች ክልከላዎችም መካተታቸውን አንስተዋል። ከእነዚህም መካከል የተቋማቱ ሠራተኞች “ከሸሚዝ በላይ” የሚሆን የአንገት ጌጥ እንዲሁም የእጅ ጌጥ እንዳይጠቀሙ የተቀመጠው ክልከላ ይገኝበታል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ “ከጌጣ ጌጥ ጋር ተያይዞ ለሴቶች ጆሮ ጌጥ ይፈቀዳል። ነገር ግን ወደታች ያልወረደ እዚያው ላይ ልጥፍ የሚል [መሆን አለበት]። በተለይ በጆሮ ዙሪያ ላይ የሚደረግ ጆሮ ጌጥ አይፈቀድም። ወንድ በምንም አይነት የጆሮ ጌጥ እንዲያደርግ አይፈቀድም” ሲሉ በረቂቁ ላይ የተቀመጡ ሌሎች ክልከላዎችን ጠቅሰዋል።

አክለውም፤ “በተለይ በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ . . . ምንም ዓይነት ንቅሳትም ሆነ ሌላም በሥዕል ተጠቅሞ ማስተናገድ አይቻልም ብሎ ደንባችን አግዷል” ብለዋል። ይሁንና ከንቅሳት ጋር በተያየዘ የሚነሱ የባህል ጉዳዮች የደንቡን መጽደቅ ተከትሎ በሚወጣ መመሪያ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

በረቂቁ ላይ ያሉ ደረጃዎች እና ክልከላዎች የሆቴል እና መሰል አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሁሉንም ተቋማት እንደሚመለከት አቶ ሃፍታይ ተናግረዋል። ከእነዚህ ተቋማት መካከል ሆቴሎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ምሽት ቤቶች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ጂሞች እንዲሁም የስቲም እና ሳውና አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚገኙበትም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው ደንብ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚተላለፉ ተቋማት በ15 ቀናት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ ምክትል ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ተቋሙ በሚሰጠው ጊዜ ውስጥ ማስተካከያ የማይወስድ አገልግሎት ሰጪ የ50 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልበትም አስረድተዋል።

በተቋማቱ ላይ የሚጣለው ቅጣት የተለያዩ እርከኖች እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ሃፍታይ፤ “ተቋሙ ከቅጣት በኋላም ካላስተካከለ የማሸግ እርምጃ ይወሰዳል። አሽጎ ብቻ መተው ሳይሆን [ከዘርፉ] እስከማሰናበት የሚደርስ ሥልጣን የሚሰጥ ደንብ ነው” ሲሉ የሚወሰደውን የመጨረሻ እርምጃ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጀው ይህ ረቂቅ ደንብ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል። ከውይይቱ የተገኙ ሀሳቦች ተካተው ረቂቁ ለአስተያየት ወደ ከተማዋ ፍትህ ቢሮ እንደሚላክ ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ሃፍታይ ገልጸዋል። ደንቡ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ለአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ነው።

በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የምግብ እና የመጠጥ አገለግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሴት የመስተንግዶ ሠራተኞች ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን እንዲለብሱ እንደሚገደዱ ሲነገር ቆይቷል።

ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ የከተማው መስተዳደር ይህንን ሁኔታ የሚያስተካክል እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ ጥሪዎች ከበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።