
7 ታህሳስ 2023, 15:53 EAT
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት የሩሲያ የደኅንነት ቢሮ ለዓመታት ፖለቲከኞች እና ሌሎች በማኅብረሰቡ ውስጥ እውቅና ያላቸው ሰዎች ላይ የበይነ መረብ (ሳይበር) ጥቃት ሲፈጽም ነበር አለ።
የዩኬ መንግሥት ከሩሲያው የደኅንነት ቢሮ ኤፍኤስቢ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ቡድን በሳይበር ጥቃት እአአ 2019 የተደረገው የምርጫ ሰነድን ጨምሮ በርካታ መረጃዎችን ሰርቋል ብሏል።
የሩሲያ መንግሥት ግን በእንደዚህ ዓይነቶቹ ተግባራት በፍጽም እጁ እንደሌለበት በመግለጽ አስተባብሏል።
በሩሲያ የሳይበር ጥቃት ዒላማ ውስጥ ገብተዋል ከተባሉት መካከል የሕዝብ እንደራሴዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የምርምር ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች በማኅብረሰቡ ውስጥ እውቅና ያላቸው ሰዎች ይገኙበታል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊዮ ዶከርቲይ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በዩኬ የሩሲያ አምባሳደር ለማብራሪያ መጠራታቸውን እና የኤፍኤስቢ ባልደረባን ጨምሮ ሁለት ግለሰቦች ላይ እገዳ መተላለፉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።
የሳይበር ጥቃቱ የሚፈጸመው ዒላማ የተደረጉ ሰዎች ላይ ዝርዝር ጥናት በማድረግ እና ተጠቂዎቹ የሚያምኗቸው ሰዎችን መስሎ በመቅረብ ኢሜይላቸውን በመጥለፍ ነው።
ይህ ሴንተር 18 የተባለው ከኤፍኤስቢ ጋር ቅርበት ያለው ቡድን ከእአአ 2015 ጀምሮ በዩኬ ፖለቲከኞችን እና ተዋቂ ሰዎችን ዒላማ ሲያደርግ ቆይቷል የተባለ ሲሆን፣ ይህ ቡድን አሁንም በሳይበር ጥቃት ሥራው ቀጥሎ እንደሚገኝ ይታመናል።
የዩኬ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው አሜሪካም በተመሳሳይ በዚህ ቡድን ላይ እግድ ትጥላለች ተብሎ ይጠበቃል።
- “የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” – አቶ ታዬ ደንደአ7 ታህሳስ 2023
- በአማራ ክልል ወራትን ያስቆጠረው ግጭት ዋነኛ ተዋናይ ፋኖ ፍላጎቱ ምንድን ነው?7 ታህሳስ 2023
- በአዲስ አበባ አስተናጋጆችን “የተራቆተ” ልብስ የሚያስለብሱ ሆቴሎችን ከ50 ሺህ ብር እስከ ማገድ የሚቀጣ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀ6 ታህሳስ 2023
የምዕራባውያን መንግሥታት ኃላፊዎች “ሩሲያ የዩኬን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ዒላማ እያደረገች ነው” ይላሉ።
ከሩሲያ መንግሥት የደኅንነት ተቋም ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው ቡድን በዘመቻ መልክ በዩኬ ላይ የሳይበር ጥቃቶችን ቢፈጽምም የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሂደት በማወክ ላይ ግን ስኬታማ አልነበረም ተብሏል።
“ይህ ቡድን ከፍተኛ መረጃ አከማችቷል። ይህ መረጃ ምዕራባውያንን በተለያየ መልኩ ለመጉዳት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው” ብለዋል ምዕራባውያኑ ኃላፊዎች።
የስኮትላንድ ቀዳሚ የሆነው ስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲን በመወከል የምክር ቤት አባል የሆኑት ስቲዋርት ማክዶናልድ ከወራት በፊት ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ከኢሜይል አድራሻቸው መረጃ መስረቁን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በቡድኑ የሳይበር ጥቃት ዒላማ ከሆኑት መካከል ሌላኛው የቀድሞ የዩኬ የደኅንነት ቢሮ ኤምአይ6 ኃላፊ ሰር ሪቻርድ ዲርላቭ ናቸው።
ከአንድ ዓመት በፊት ለዩኬ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ጦር ሠራዊት የግንኙነት ደኅንነት አገልግሎት የሚሰጠው ጂሲኤችኪው ከኢራን እና ሩሲያ በኢሜይል ላይ ያሉ መረጃዎችን ዒላማ ስለዳረጉ ጥቃቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
በወቅቱ ጂሲኤችኪው በመረጃ መንታፊዎች ጥቃት የገጠማቸውን ሰዎች አሳውቆ ነበር።
ዩኬ በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት ልታካሂደው የምትችለው ምርጫ እንዲሁም የአሜሪካ የ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመረጃ መንታፊዎች ዒላማ ሊደረግ እንደሚችል ይገመታል።
እአአ 2016 ላይ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት የሩሲያ ደኅንነት ቢሮ አካል የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ የነበሩትን የሂላሪ ክሊንተን የምርጫ ቅስቀሳ ኢሜይል መረጃዎን መንትፎ ይፋ አድርጎ ነበር።