በጋዛ የሐማስ ኃላፊ የያህ ሲንዋር
የምስሉ መግለጫ,በጋዛ የሐማስ ኃላፊ የያህ ሲንዋር

7 ታህሳስ 2023, 16:43 EAT

የእስራኤል መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ለተፈጸመባት ጥቃት ዋነኛ ተጠያቂ ነው ያለችውን በጋዛ የሐማስ ኃላፊ የሆነውን ያህያ ሲንዋር መኖሪያ ቤትን ጦሯ መክበቡን አስታወቀች።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሲንዋርን “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንይዘዋለን” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር በርካታ ተፈናቃዮችን በያዘው እና የያህያ ሲንዋር መኖሪያ ቤት ይገኝበታል በተባለው ኻን ዩኒስ መሃል መድረሱን አስታውቋል።

“. . . ጦራችን በጋዛ ሰርጥ የትም መድረስ እንደሚችል ተናግሬ ነበር። አሁን የሲንዋርን ቤት ከበናል” ብለዋል በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቢቢ ተብለው የሚጠሩት ኔታኒያሁ።

ሲንዋር በጋዛ የሐማስ ፖለቲካዊ ክንፍ ኃላፊ ሲሆን ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ካቀነባቡሩት መካከል ቀዳሚው መሆኑን እስራኤል ስትገልጽ ቆይታለች።

በዚህም ሲንዋር በእስራኤል ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሰው ሆኖ ቆይቷል። ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር አዛዥ “ያህያ ሲንዋር . . . ሞት የማይቀርለት ሰው ነው” ሲሉ አውጀው ነበር።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሔርዚ ሃሌቭ “ይህ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጠው ያህያ ሲንዋር ነው። ስለዚህ እርሱ እና በስሩ ያሉ አባላቱ የሚራመዱ ሙቶች ናቸው” ብለው ነበር።

የእስራኤል ደኅንነት መረጃዎች ሲንዋር በጋዛ ልክ እንደ የሸረሪት ድር ከመሬት በታቸ ከተዘረጉት ዋሻዎች በአንዱ ከግል ጠባቂዎቹ ጋር ተደብቆ፤ የስልክ መስመሬ ሊጠለፍ ይችላል በሚል ስጋት ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳያደርግ እንደሚገኝ ያሳያሉ።

የሲንዋር ትክክለኛ መገኛ የት እንደሆነ የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የያህ ሲንዋር እና ሌሎች የሐማስ የፖለቲካ እና ጦር ከፍተኛ አመራር የሆኑ ሰዎች በኻን ዩኒስ በሚገኙ ዋሻዎች ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙ ይገመታል።

የእስራኤል ጦር በዚህ አካባቢ የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ያጠናከረ ሲሆን፤ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው አል-ቃስም ብርጌድም በኻን ዩኒስ ከእስራኤል ጦር ጋር ከፍተኛ ውጊያ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ቃል አቀባይ ሪር አድርሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በደቡብ አቅጣጫ የምትገኘው የጋዛ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ኻን ዩኒስ የትኛውም ክፍል ሲንዋርን ለመያዝ ሲባል ዒላማ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብለዋል።

ሃጋሪ “ሲንዋር ከምድር በታች (ዋሻ ውስጥ) ተደብቆ ይገኛል። የት እንደሚገኝ እና በምናቀው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም። ሥራችን ሲንዋርን መያዝ እና መግደል ነው” ብለዋል።