
ከ 5 ሰአት በፊት
ኬንያ 1ሺህ 500 ዜጎችን ለእርሻ ሥራ ወደ እስራኤል ልትልክ መሆኑን የአገሪቱ የሠራተኛ ሚንስቴር አስታወቀ።
የአገሪቱ መንግሥት ለእርሻ ሥራ የሚሄዱት ዜጎች በየሦስት ዓመቱ በሚታደስ ውል በየወሩ የተጣራ 1ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር እየተከፈላቸው ይሠራሉ ብሏል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ የማላዊ መንግሥት 221 ወጣቶችን ለተመሳሳይ ሥራ ወደ እስራኤል የላከ ሲሆን ተጨማሪ 5ሺህ ወጣቶችን እንደሚልክም አስታውቋል።
እስራኤል ከሐማስ ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች አገሪቱን ጥለው ወጥተዋል። አንዳንድ አሃዞች እንደሚጠቁሙት አብዛኛዎቹ ታይላንዳውያን የሆኑ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ስደተኛ የጉልበት ሠራተኞች እስራኤልን ጥለው ወጥተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፍልስጤማውያን በጉልበት ሥራ እንዳይሰማሩ በመከልከሏ እስራኤል ከፍተኛ የሠራተኛ እጥረት ገጥሟታል።
በዚህም የተነሳ እስራኤል የጉልበት ሠራተኛ ፍላጋ ፊቷን ወደ አፍሪካ አዙራለች።
በኬንያ የእስራኤል አምባሳደር ማይክል ሎተም አገራቸው ከኬንያ እና ማላዊ በተጨማሪ በታንዛኒያ የሠራተኛ ቅጥር መጀመሯን እና በቀጣይ ደግሞ ከኡጋንዳ ቅጥር እንደምታደርግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደ አምባሳደሩ ማብራሪያ የሠራተኛ እጥረት የተከሰተበት ሌላኛው ምክንያት የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ወደ 360 ሺህ የሚጠጉ ተጠባባቂ የጦር ሠራዊት አባላት ለግዳጅ በመጠራታቸው ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የእስራኤል የግብርና ሚንስቴር አገሪቱ ከ30-40ሺህ ሠራተኞችን እንደምትፈልግ ተናግረው ነበር።
በኬንያ ዜጎች ለሥራ ወደ እስራኤል የመሄድ ዜና የተለያየ አስተያየትን አሰንዝሯል። አንዳንዶች ወጣቶች የተሻለ ገንዘብ የሚያገኙበት ዕድል ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የደኅንነት ስጋትን አንስተው ይከራከራሉ።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ደንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ከተገደሉት አንድ ሺህ 200 ሰዎች መካከል 32 የሚሆኑት በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ የታይላንድ ዜጎች ሲሆኑ ሌሎች ተጨማሪ የታይላንድ ዜጎች ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተቺዎች ሠራተኞቹ ወደ እስራኤል ከተጓዙ በኋላ በእስራኤል ስለሚጠብቃቸው ሕይወት አጥብቀው ይጠይቃሉ።
እአአ 2018 ላይ ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ በእስራኤል በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ ስደተኞች የሥራ ቦታቸው ደኅንነቱ ያልተጠበቀ መሆኑን፣ ንጽሕና በሌለው ቦታ እንደሚኖሩ፣ ለረዥም ሰዓታት እንዲሰሩ እንደሚገደዱ፣ ሙሉ ክፍያ የማይከፋላቸው እንዳሉ እንዲሁም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ምክንያቱ በግልጽ ባልተደረገ ሁኔታ ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጦ ነበር።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲሁ ከዚህ ቀደም እስራኤል ስደተኛ የጉልበት ሠራተኞችን የምትይዘበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።
እስራኤል ግን የአገሪቱ ዜጎች እና የውጭ አገር ሠራተኞች በሥራ ቦታ ላይ ተመሳሳይ የቅጥር ሁኔታ ነው ያላቸው ስትል ትከራከራለች።
የሥራ ዕድሉን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጥሩት ደግሞ በኬንያ የሥራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ከፍ ባለበት እና ሰዎች በኑሮ ውድነት በሚቸገሩበት ወቅት ከእስራኤል በኩል የመጣው ቅጥር አዎንታዊ ነው ይላሉ።
እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በኬንያ ያለው የሥራ አጥ ምጣኔ 5.5 በመቶ ነው።
በኬንያ የእስራኤል አምባሳደር ሠራተኞቹ ግጭት ባለባቸው የድንበር አካባቢዎች እንደማይሰማሩ ተናግረዋል።
ለእርሻ ስራ እስራኤል ከደረሱት መካከል የማላዊ ዜጋ የሆነው የ27 ዓመቱ አንድሩ ቹንጋ አንዱ ነው። አንድሩ እስራኤል ከደረሰ ሁለት ሳምንታት ማለፋቸውን ገልጾ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ሁለት የአገሩ ዜጎች ጋር በመካከለኛው እስራኤል ባለ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ተከራይተው እንደሚኖሩ ይናገራል።
“የመጣሁት ለገንዘብ ብዬ ነው። አገሬ ስገባ ሚሊየነር እሆናለሁ” ብሏል የመጀመሪያ ሳምንት ሥራውን አረም በማስወገድ የጀመረው ወጣት።
በቅርቡ በእስራኤል ሥራ የጀመረው ሌላኛው የማላዊ ዜጋ የሆነው ጃሚሰን ኩፕታሞዮ የሥራ ዕድሉን በማግኘቱ እጅጉን መደሰቱን ገልጾ ለቤተሰቡ ጥሩ ገንዘብ መላክ እንደሚችል ይናራል።
“በማላዊ ሥራ የለም። ክፍያውም ያነሰ ነው። በእስራኤል ስላለው ጦርነት ቀድሜ አውቃለሁ። ጦርነቱ ያለው በመላው እስራኤል አይደለም። ብዙ ሐሰተኛ መረጃዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሉ” ካለ በኋላ በእስራኤል ለአምስት ዓመታት ለመቆየት እንዳሰበ እና በየዓመቱ ለእረፍት ወደ ማላዊ የመሄድ እቅድ እንዳለው ለቢቢሲ ተናግሯል።