
ከ 6 ሰአት በፊት
ከየመን ጠረፍ እስከ ጋዛ ሰርጥ ያለው ርቀት ከ1600 ኪሎ ሜትር በላይ ይርቃል፤ ቢሆንም ባለፈው እሑድ ቀይ ባሕር ላይ የሆነው ነገር በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ያለውን ጦርነት ሊያባብሰው የሚችል ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ ክንፍ የሆነው ማዕከላዊ ዕዝ እንደሚለው በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማፂያን በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ነው።
አማፂያኑ ጥቃቶች የሚፈፀሙት ተቀጣጣይ ድሮኖች እና ፀረ-መርከብ ሚሳዔሎችን በመጠቀም መሆኑን ማዕከላዊው ዕዝ ገልጿል።
የአሜሪካ ባሕር ኃይል በአካባቢው ሚሳዔል አምካኝ መሣሪያ የታጠቀ መርከብ አለው። መርከቡ ዩኤስኤስ ካርኒ ይባላል። በቅርቡ ከተቃጡ ጥቃቶች ሦስቱን ድሮኖች መመከት ችሏል።
ነገር ግን ሌሎች ከአማፂያኑ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ዒላማቸውን ቢመቱም ሰዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም።
ፔንታገን “እነዚህ ጥቃቶች በዓለም አቀፍ ንግድ እና የባሕር ደኅንነት ላይ ስጋት የሚደቅኑ ናቸው” ሲል መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው አክሎ እነዚህ ጥቃቶች “በኢራን መንግሥት እንደሚደገፉ እምነት አለን” ይላል።
እነዚህ ጥቃቶች ከየት ነው እየተሰነዘሩ ያሉት የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው።
ጥቃቶቹ የሚመጡት አህጉረ አፍሪካን ከአረቢያ ባሕረ ገብ መሬት ባብ ኤል ማንደብ ወሽመጥ ነው። ይህ ወሽመጥ በየዓመቱ 17 ሺህ መርከቦች ይመላለሱበታል፤ የዓለማችን 10 በመቶ ንግድ መተላለፊያም ነው።
በሱዊዝ ካናል አድርጎ በደቡብ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ የሚያመራ ማንኛውም መርከብ ይህንን ወሽመጥ ማቋረጥ አለበት። ወሽመጡ ለየመን ወደብ እጅግ የቀረበ ነው።
ከጥቃቱ ጀርባ ያለው ምንድን ነው? ከጋዛ ጋርስ ምን አገናኘው?
የቀይ ባሕር ጠረፍን ጨምሮ ሕዝብ የሚበዛባቸው የየመን ክፍሎች በአውሮፓውያኑ 2014 የየመንን መንግሥት በገለበጡት የሁቲ አማፂያን እጅ ሥር ነው።
እነዚህ በጎሳ የተከፋፈሉ አማፂያን በኢራን እንደሚደገፉ ይነገራል። ኢራን ለአማፂያኑ የመሣሪያ እና የሥልጠና ድጋፍ ትሰጣለች።
ለሁቲ አማፂያን ብቻ ሳይሆን በጋዛው ለሚገኘው ሐማስ እና ለሊባኖሱ ሄዝቦላህ እንዲሁ ድጋፍ እንደምታደርግ ይታመናል።
- የአሜሪካ ባሕር ኃይል የእስራኤላዊያንን መርከብ አግተው የነበሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ28 ህዳር 2023
- የጃፓን ዕቃ ጫኝ መርከብ ቀይ ባሕር ላይ በየመን ሁቲ አማጺያን ታገተ20 ህዳር 2023
- የአሜሪካ ጦር መከርብ ቀይ ባሕር ላይ ከየመን የተተኮሱ ድሮኖችን መትቶ መጣሉን ገለጸ4 ታህሳስ 2023

ሁቲዎች የጠነሰሱት መፈንቅለ መንግሥት ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርቶ የመን በግጭት መታመስ ከጀመረች ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል።
በርካቶች በዚህ ግጭት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
ኢራን ሁቲዎችን የምትደግፍ ሲሆን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተበባሩት አረብ ኢምሬቶች (ዩኤኢ) በአንድ ወገን ሆነው በአሜሪካና በዩናይትድ ኪንግደም ተደግፈው በ2015 ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
አገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውን መንግሥት ወደ ሥልጣን ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም።
በዚህ ጦርነት ወቅት ሁቲዎች በርካታ ረዥም ርቀት ተጓዥ ሚሳዔሎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩኤኢ እና የመን የተኮሱ ሲሆን፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ከተሞች እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ዒላማ ሆነዋል።
መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ከተቀሰቀሰው የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት በኋላ ሁቲዎች “በጋዛ ላሉ ወንድሞቻችን” ድጋፍ እንሰጣለን ብለው ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ተኩሰዋል።
ሚሳዔሎቹ ዒላማቸውን ሳይመቱ በአሜሪካ የጦር መርከብ አየር ላይ ሳሉ እንዲከሽፉ ተደርገዋል።
ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አለው ያሉትን የትኛውንም ዓይነት መርከብ ዒላማ በማድረግ ላይ ናቸው።
አማፂያኑ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ‘ዘ ጋላክሲ ሊደር’ የተሰኘ የጭነት ማጓጓዣ መርከብን በሄሊኮፕተር ተከታትለው በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ይታወሳል። የትኛውም የእስራኤል መርከብ የባሕር ጠረፍ በኩል ሊያልፍ እንደማይችል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ባለፈው እሑድ መርከቦች ጥቃት የደረሰባቸው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ስለታመነ ቢሆንም የእስራኤል ጦር ግን ይህን ያስተባብላል።
ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ከሃብታም እስራኤላውያን ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ የግል መርከቦች በሥፍራው ያልፋሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ “የትኛውንም ዓይነት አስፈላጊ የሚባል እርምጃ ለመውሰድ ከወዳጆቿ ጋር እየመከረች እንደሆነ” አስታውቃለች።
ምንም እንኳ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት ከአካባቢው ወጥቶ እንዳይስፋፋ ዋሽንግተን ስጋት ቢኖራትም፣ የየመን ሁቲዎች ጥቃት ማድረሳቸውን ከቀጠሉ ዩናይትድ ስቴትስ የሚሳዔል ምንጭ የሆኑ ሥፍራዎችን ልትመታ ትችላለች።
ይህ ከሆነ ሁቲዎችን የምትደግፈው ኢራን የአፀፋ እርምጃ ልትወሰድ ትችላለች የሚል ስጋት አለ። ይህ ሆነ ማለት አሜሪካ ፍፁም የማትሻው ከኢራን ጋር የሚደረግ ቀጥተኛ ጦርነት ተነሳ ማለት ነው።
ለጊዜው ኢራንም ሆነች አሜሪካ ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ መግባትን የሚደግፉት ሐሳብ አይደለም።