ቱኋን

ከ 5 ሰአት በፊት

የቱኋን ወረርሽኝ ስጋት በሆነባት ፈረንሳይ አዛውንቶችን “ቱኋን እንጥፋላችሁ” በማለት በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንዳጭበረበሩ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በፈረንሳይ ስትርራስቦርግ ከተማ የታሰሩት ግለሰቦች አገለግሎቱ የማያስፈልጋቸውን ሰዎች አጭበርብረዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች ኢላማ ባደረጓቸው ሰዎች ቤት እየተዘዋወሩ ቱኋን ያጠፋል የሚሉትን የውሸት ድርጊት በመፈጸም የተጋነነ ክፍያ ሲቀበሉ እንደነበር በፈረንሳይ የስትርራስቦርግ ከተማ ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በዚህ መልክ 48 ሰዎችን ያጭበረበሩ ሲሆን አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ90 በላይ የሆኑ ሴቶች አዛውንቶች ናቸው ሲል ፖሊስ አክሏል።

በቅርብ ወራት ውስጥ በፈረንሳይ የቱኋኖች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩ ተዘግቧል።

በዚህም ሳቢያ በሀገሪቱ ትልቅ ስጋት የተፈጠረ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ባለስልጣናት መፍትሄ እያፈላለጉ ይገኛሉ።

ይህ ፈረንሳይን ያሰጋት የቱኋን ወረርሽኝ ከጤና ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችን እንዳያስከትል የነፍሳት ጥናትና የጤና ባለሙያዎች አሳስበዋል።

ታዲያ አጭበርባሪዎቹ ሁኔታው ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። እንደ ባለስልጣናት ገለጻ ሀሰተኛ ቱኋን አጥፊዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ግለሰቦች ኢላማ ያደረጓቸው ሰዎች ጋር በመደወል በአከባቢያቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱኋን እንደሚገኝ ይነግሯቸዋል።

በመቀጠል ወደ ስዎቹ ቤት የጤና ባለሙያ መስለው በመሄድ ሀሰተኛ የማጥፊያ ርጭት ያካሂዳሉ።

ከርጭቱ በኋላ ደግሞ “ይኼ ቆዳችሁ ጋር ቱኋን ድርሽ እንዳይል የሚያደርግ ነው” በማለት ቅባት እንደሚሰጧቸው ታውቋል። ቅባቱ ለእዚህ አይነት አገለግሎት የማይውል መደበኛ የባሕር ዛፍ ሽታ ያለው የቆዳ መንከባበከቢያ ቅባት ነው።

በዚህም “አገልግሎት” ኢላማ ካደረጓቸው ሰዎች ከ300 እስከ 2ሺህ 100 ዩሮ እንደሚቀበሉም ተደርሶበታል።

በአጠቃላይ እስካሁን 9 ሰዎች ተጭበርብረናል ሲሉ ለፖሊስ አመልክተዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪቀቹ ላይ ክትትል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በስትራስቦርግ ከተማ ከአንድ ሰው ቤት ቱኋን አጥፍተናል ብለው ሲወጡ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

በፓሪስ የተከሰተው የተኋን ወረርሽኝ ወደ ለንደን በተዘረጋው የትራንስፖረት መስመር አማካኝነት እንዳይዛመት ተፈርቷል።

ባለፈው የለደን ከንቲባ ሳዲቅ ካሃን የሕዝብ ማመላለሻ መስመሮች “የስጋታችን ምንጭ ሆነዋል” ብለዋል።

ጨምሮ ችግሩ ወደ ለንደን እንዳይመጣ ከፓሪሱ አቻቸውና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን ከንቲባው ተናግረዋል።