
የጽሁፉ መረጃ
- ፀሐፊ,የቢቢሲው ሪፖርተር አድናን ኤል-ቡርሽ
- የሥራ ድርሻ,ቢቢሲ አረብኛ
- ዘገባው ከኻን ዮኒስ፤ ጋዛ
- ከ 6 ሰአት በፊት
ጂንስ ሱሪ የለበሱ እና ነጠላ ጫማ የተጫሙ ወጣት ፍልስጤማውያን ኻን ዮኒስ ከሚገኘው ናስር ሆስፒታል ፊት ለፊት ቀብር አስፈጻሚ መስለው በዝምታ ቆመዋል።
እስራኤል ከኅዳር 21 ጀምሮ ደቡብ ጋዛን በቦምብ መደብደብ ከጀመረች ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
በሆስፒታሉ የድንገተኛ በር ላይ ዛሬም ሰዎች በሐዘን እና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ይታያሉ።
የሐኪሞች የደንብ ልብስ የለበሱ ወንዶች ከሆስፒታሉ ደጃፍ ላይ ሆነው በመጠባባቅ ላይ ናቸው። በስቃይ ስሜት ውስጥ የቆዩት ሰዎች ተሰላችተዋል።
ድንገት ሰዎች ሲጯጯሁ በርካታ ወንዶች ተሰባሰቡ። ጡሩምባውን ካለማቋረጥ የሚያስጮህ እና መብራቱን ብለጭ ድርግም የሚያደርግ መኪና በፍጥነት መጥቶ ከሆስፒታሉ መግቢያ በር ላይ ይቆማል።

- ጋዛ፡ “የት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት? እንዲህ ሆነን የት እንሂድላቸው?”7 ታህሳስ 2023
- የእስራኤል ጦር የሐማስ ኃላፊ የሆነው የያህያ ሲንዋር መኖሪያ ቤትን መክበቡን አስታወቀ7 ታህሳስ 2023
- ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ 100 ሺህ ሕንፃዎች የወደሙባት የፍርስራሽ ክምሯ ጋዛ በሳተላይት ዕይታ2 ታህሳስ 2023
ከመኪናው አንድ ወጣት ወንድ ከወጣ በኋላ ቃሬዛ ላይ ተደርጎ በፍጥነት ወደ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ።
እንደገና ሌላ መኪና በአቧራ ተሸፍኖ መጣ። አሁን ደግሞ ከመኪናው የወረደው ትንሸዬ ልጅ ነበር። አራት ወይም አምስት ዓመት ቢሆነው ነው።
በቀጣይ ቀን መሃል ጋዛ ከተማ ሳማህ ኢልዋን የተባለች የስድስት ልጆች እናት ስትለምን ትሰማለች።
“ለመላው ዓለም እና ለአረቡ ዓለም መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ትላለች።
ሳማህ “ለመላው ዓለም መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን ምንም አላጠፋንም” እያለች ባዶ የውሃ መያዣ ኮዳ የያዙ እጆቿን ታወራጫለች።
ሳማህ ኢልዋን አምስት ሴት እና አንድ ወንድ ልጆቿ በውሃ ጥም መቃጠላቸውን ትገልጻለች።
“ልክ እንደ ድመት እና ውሾች ሆነናል። ለነገሩ ድመቶች እና ውሾች መጠለያ ያገኛሉ። እኛ ምንም የለንም። በመንገድ ላይ ወድቀን መሄጃ ጠፍቶናል።”

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በጋዛ ሕይወት የተለየ ሆኗል።
በዚያ ዕለት ጥቃት በአውሮፓ ኅብረት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር ዘልቆ በመግባት ቢያንስ 1200 ሰዎችን ገድሎ ከ240 በላይ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል።
ጥቃቱ እስራኤልን በእጅጉ አስቆጣ። ከጥቃቱ በኋላ እስራኤል ለሳምንታት ጋዛን በከባድ የአየር ጥቃቶች ስትደበድብ ቆየች። ከዚያም የምድር ኃይሏን ወደ ሰሜን ጋዛ አንቀሳቀሰች።
በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ15800 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ይላል።
ሁለቱ ኃይሎችን ለማደራደር የተደረገው ከፍተኛ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ኳታር ለሰባት ቀናት ለጦርነቱ ፋታ እንዲሰጥ እስራኤል እና ሐማስን አስማምታ ነበር።
በዚህ ተኩስ በማቆም ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ስምምነት በተደሰበት ወቅት እስራኤል እና ሐማስ የታሳሪዎች እና ታጋቾች ልውውጥ ማድረግ ችለው ነበር።
ተኩስ ለማቆም ተደርሶ የነበረው ስምምነት ማብቃትን ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ጦርነት ተመልሰዋል።

በዚህ ጦርነት መሃል በመካከለኛው ጋዛ ከሚገኙት ቤተሰቦቼ ተለይቼ ብቻዬን ኻን ዮኒስ ነው ያለሁት።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኻን ዮኒስ የሳተላይት ማሰራጫ ተሸካሚ ለሆነው ተሸከርካሪያችን የተሻለ ደኅንነት ያለበት ቦታ ነበር።
ሁልጊዜም ቢሆን በጋዜጠኝነት ሙያዬ ኩራት ይሰማኝ ነበር። አሁን ላይ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደሌለኝ እየተሰማኝ ነው።
ቤተሰቤን ለማየት በየዕለቱ ወደ መካከለኛው ጋዛ እጓዝ ነበር። አሁን ግን እስራኤላውያኑ አንደኛውን መንገድ ዘግተውታል። ቀሪው ወደ መካከለኛው ጋዛ የሚወስደው መንገድ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው።
ትውልድ እና ዕድገቴ ሰሜን ጋዛ ነው። ይሁን እንጂ በእስራኤል ጦር “ደኅንነቱ የተጠበቀው ደቡብ ጋዛ ነው” በሚል ወደ ደቡባዊ ክፍል እንድንዘዋወር ትዕዛዝ ከሰጠን በኋላ ከቤተሰቤ ጋር ተፈናቅያለሁ።
አሁን ደግሞ በኻን ዮኒስ “አደገኛ የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ” እንደሚያደርጉ የገለጹ ሲሆን በደቡብ አቅጣጫ ወደ ግብፅ ድንበር ራፋህ እንድንሸሽ ማሳሰቢያ እየሰጡን ነው።
ይህ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ እኔ ላይም ሆነ ቤተሰቤ ላይ ብዙ ነገሮች ቢከሰቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ግራ በመጋባት ስሜት የምይዘው የምጨብጠው የጠፋኝ አሁን ገና ነው።
በዝርዝር በማቀድ የቤተሰቤን ደኅንነት ስጠብቅ ቆይቻለሁ። አሁን ግን ምን መወሰን እንዳለብኝ ግራ ተጋብቻለሁ።
ቤተሰቤ ሰላም ይሆናል በሚል ተስፋ ወደ ራፍህ ሄጄ በሙያዬ ልቀጥል? ወይስ የከፋው ቢመጣም አብሮ መሞት ይሻላል በሚል ወደ ቤተሰቤ በመመለስ ሥራዬን ልተው?
እንደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ መግባትን ለማንም አልመኝም።