ሀንተር ባይደን
የምስሉ መግለጫ,ሀንተር ባይደን

ከ 2 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን ዳግም ክስ ተመሠረተበት።

የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከእአአ ከ2016-19 ድረስ ባሉት ዓመታት ግብር ለላመክፍል ቢያንስ 1.4 ሚሊዮን ዶላር አሽሽቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

የ53 ዓመቱ ሃንተር ባይደን ከዚህ ቀደም ጦር መሣሪያ ለመግዛት የሐሰት ሰነድ አዘጋጅቷል በሚል በዴልዌር ግዛት ተከሶ ነበር።

ሃንተር ባይደን ከጦር መሳሪያ ግዢው ጋር በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል። በካሊፎርኒያ በተከፈተበት የግብር ማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 17 ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል።

ዐቃቤ ሕግ ሃንተር ባይደን ገንዘቡን “አደንዛዥ ዕጽ ለመግዛት፣ ለሴቶች ክፍያ ለመፈጸም፣ ለቅንጡ ሆቴሎች እና መኪኖች እንዲሁም አልባሳት ላይ ወጪ” አድርጓል ብሏል።

የክስ መዝገቡ ሃንተር ከእአአ ከ2016-19 ድረስ 188 ሺህ ዶላር ለመዝናኛ እንዲሁም ከ683 ሺህ ዶላር በላይ “ለተለያዩ ሴቶች” ክፍያ መፈጸሙን ያሳያል።

በ2018 ላይ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ የተመለከተ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ በዓመቱ ውስጥ 383 ሺህ ዶላር ለሴቶች ክፍያ የፈጽሞ፣ 151 ሺህ ዶላር ደግሞ ለአልባሳት ወጪ አውጥቷል።

በፕሬዝዳንቱ ልጅ ላይ የቀረበው ክስ ከ2016 እስከ 2020 ድረስ በጠቅላላው ከግብር በፊት 7 ሚሊዮን ዶላር ቢከፈለውም ከ2016 እስከ 2019 ድረስ ግብር ሳይከፍል ቀርቷል ይላል።

ሃንተር ግን ክሶች የተደራረቡብኝ የፕሬዝዳንት ልጅ በመሆኔ ነው ይላል።

የሃንተር ጠበቃ አቤ ሎዌል “የሃንተር ስም ከባይደን ጋር የተያያዘ ቢሆን ኖሮ በዴልዌር እና ካሊፎርኒያ ክሶቹ ባልተመሠረቱበት ነበር” ብለዋል።

ሃንተር ባይደን እአአ 2020 የነበረበትን ውዝፍ ግብር ከግል ጠበቃው ተበድሮ ከፍሏል።

ዐቃቤ ሕግ ሃንተር እአአ 2018 ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተከፋይ ቢሆንም፣ ግብር ለመክፈል ግን ምንም አይነት ፍላጎት አላሰየም ይላሉ።

የባይደን ልጅ ላይ የቀረቡት ክሶች ሃንተር ግብር ሳይከፍል ከመቅረቱም በተጨማሪ ለግል መዝናኛው ብሎ የሚያወጣቸውን ወጪዎች የሥራ ወጪ አድርጎ ሲያስመዘግብ ቆይቷል ይላሉ።

እንደማሳያም ሃንተር 1500 ዶላር በእርቃን ዳንስ ቤት ለአንዲት ሴት የከፈለውን ክፍያ የዕደ ጥበብ ውጤት ለመገዛት የወጣ ወጪ አድርጎ መዝግቧል ይላል የክስ መዝገቡ።

ከዚህ በተጨማሪም ምንም የሥራ ጉዳይ ሳይኖረው ለሥራ በሚል ስም በርካታ ዓለም አቀፍ በረራዎችን አድርጓል ይላል መዝገቡ።

ሃንተር ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማግኘት የቻለው ከቻይናዊ ባለሃብት ጋር ኩባንያ መመሥረቱ፣ እንዲሁም በዩክሬን እና ሮሜኒያ ባለው ንግድ ነው።