የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ

ከ 2 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ ለማስተናገድ የተዘጋጀችው ሩዋንዳ በስምምነቱ መሠረት 100 ሚሊዮን ፓውንድ እንደተከፈላት ተገለጸ።

የዩኬ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ሰር ማቲው ራይክሮፍት ክፍያው የተፈጸመው ባለፈው ሚያዚያ ወር እንደነበር ለፓርላማ አባላት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተዋል። ሩዋንዳ ከዚህ ክፍያ አስቀድሞ የዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመቀበል 140 ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሏታል።

ሰር ማቲው ራይክሮፍት ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ፓውንድ በቀጣዩ ዓመት ይከፈላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ክፍያው መፈጸሙ የታወቀው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የተጀመረውን ዕቅድ ከዳር እንደሚያደርሱ ቃል ከገቡ እና የስደት ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ ከሳምንት በኋላ ነው።

ይህ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሌላ አገር የማቆየት ሃሳብ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 በቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይፋ የተደረገ ነው። በዚህ መሠረትም የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው እስከሚታይ ድረስ በሩዋንዳ የሚቆዩ ሲሆን፣ በጀልባ ድንበሮችን አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞችን ለመከላከል ያለመ ነው።

ሆኖም ይህ ዕቅድ በተደጋጋሚ በተነሱበት የሕግ ጥያቄዎች ምክንያት ተግባራዊነቱ የዘገየ ሲሆን፣ አንድም ጥገኝነት ጠያቂ እስካሁን ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ አልተላከም።

በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረትም እስካሁን ድረስ የዩኬ መንግሥት ለዚህ ዕቅድ ቢያንስ 140 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረጉ ታውቋል።

ሰር ማቲው ቀደም ብለው ክፍያውን በተመለከቱ ያሉ አዳዲስ ጉዳዮችን እንዲያብራሩ ቢጠየቁም፣ ሚኒስትሮች ዓመታዊ ወጪውን ይፋ ያደርጋሉ በማለት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ሆኖም ትናንት ሐሙስ ለአገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዳሜ ዲያና በጻፉት ደብዳቤ የገንዘቡን መሉ መጠን ይፋ አደርገዋል።

ሰር ማቲው ይህ ክፍያ ሩዋንዳ እና ዩናይትድ ኪንግድም የተፈራረሙት ስምምነት ባለፈው ወር የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረገው ዕቅድ ሊደረግ ከታሰበው የፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ቃል አቀባይ ገንዘቡ ምን ላይ እንደሚውል ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ለሩዋንዳ ልማት እና ዕደገት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ክፍያ የተፈጸመው በቀድሞዋ የአገር ውስጥ ጉዳይ ዋና ፀሐፊ የሥልጣን ጊዜ ቢሆንም የእሳቸው አጋሮች ግን የተፈረመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ይላሉ።

የገንዘቡ መጠን ይፋ በሆነበት ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በሰጡት መግለጫ የምክር ቤት አባላት ዕቅዳቸው እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ከማድረጋቸው አንድ ቀን አስቀድሞ የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትሩ ሮበርት ጄንሪክ መንግሥታቸው እያደረገ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያን በመቃወም ሥልጣናቸውን ለቀዋል። ማሻሻያው ወደ ውድቅት የሚመራ ነው ሲሉም ተችተዋል።

በተቀራኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ማሻሻያው ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ እንዳይዘዋወሩ እክል የሚፈጥረው የሕግ ተቃርኖ እንዲያበቃ ያደርጋል ብለዋል።

አዲሱ የጥገኝነት ጠያቂዎች ረቂቅ ፍርድ ቤት ሩዋንዳን ለጥገኝነት ጠያቂዎች ደኅንነቷ የተጠበቀች አገር አድርገው እንዲቆጥሯት ይጠይቃል። በተጨማሪም ሚኒስትሮች የሰብአዊ መብት አዋጆችን ከግምት እንዳያስገቡ ይደነግጋል።

ሆኖም የአወሮፓ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን ችላ እንዲሉ ሥልጣን አይሰጣቸውም።

በቀጣዩ ሳምንት ወደ ምክር ቤት የሚመለሰው ማሻሻያ የተደረገበት ረቂቅ ሕግ ቀደም ብሎ ከተለያዩ ጉዳዮች አንጻር ተቃውሞ ገጥሞታል።

ከሥልጣናቸው የለቀቁት ሚኒስትር ረቂቁ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ይጻረራል ሲሉ ተቃውመውታል።