December 8, 2023 – Konjit Sitotaw
ስብሰባ ላይ መዓት ወርዶባቸው ሲመለሱ፣ ደፈጣ ደግሞ ጠበቃቸው!
የአገዛዙ ካድሬዎች እና የዙፋን ጠባቂ አራዊት ሠራዊት አዛዥ ኮሎኔል አዘዘ በዛሬው እለት በስናን ወረዳ በረዕቡ ገበያ ከተማ ማኅበረሰቡን ስብሰባ ጠርተው “ፋኖን አውግዙልን፣ እጃቸውን እንዲሰጡ አግባቡ” የሚል ዲስኩር ለማሰማት ሙከራ አድርገው ነበር።
ነገር ግን ማኅበረሰቡ በአንድ ድምጽ “ፋኖን ያስታጠቀነው እኛ ነን፤ ከዛም ማርከህ ታጠቅ ተብሎ ታጥቋል፣ ወደፊትም እንደግፈዋለን፤ ሁላችንም ፋኖን ነን። ልጆቻችን ፋኖ የሆኑት አራት ዓመት ሙሉ ልጆቻችን ለትምህርት ሄደው ሲታገቱ፣ ልጆቻችን ለሥራ ሄደው ታግተው አንድ ሚሊዮን ብር አምጡ ስንባል፣ እናቶች እና ሕጻናት በማንነታቸው ሲገደሉ፣ ወደ ዋና ከተማችን አትገቡም ስንባል… በሰላማዊ ሰልፍ ስንጠይቅ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ስትስቁብን ነበር። ስለዚኽ ፋኖ የተነሳነው ለጥያቄችን ራሳችን ምላሽ ለመስጠት ነው።”
የስብሰባው ተሳታፊዎች አክለውም “ላለፉት አራት ወራት በፋኖ መሪነት ስርቆት ጠፍቶ፣ መልካም አስተዳድር ሰፍኖ፣ የተጣለ ታርቆ በሰላም እየኖርን ነበር። እናንተ ስትመጡ ግን ይኸው ሁሉ ነገር ተበላሸ። ዓላማችሁ ሕዝብን መጠበቅ ከሆነ ከተማ ውስጥ ምሽግ የምትቆፍሩ ለምንድን ነው? እኔ የደርግ ወታደር ነኝ 18 ዓመት ስታገል ከተማ ውስጥ ምሽግ ሲቆፈር አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ጠላት ራሱ እንዲህ አያደርግም! የራሳችንን ሰላም ራሳችን እንጠብቃለን፤ እኛ እናንተ እንድትወጡልን ነው የምንፈልገው…!” የሚሉ ጠጠር ያሉ ጭብጨባና ጩኽት የታጀቡ ንግግሮችን አድርገዋል።
የአገዛዙ ቅጥረኞችም፤ በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው ወደ ደብረ ማርቆስ ሲመለሱ፣ የጠድ ላይ በተደረገ የደፈጣ ጥቃት ሙት እና ቁስለኛ መሆናቸው ተሰምቷል፤ የቆሰሉትም ስላሴ አካባቢ ባለ ካምፓቸው ውስጥ ወዳለ የህክምና ማዕላቸው እንደገቡ ተረጋግጧል።
