
8 ታህሳስ 2023, 15:24 EAT
አንድ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቀ ቪድዮ ፍልስጤማውያን ወንዶች ልብሳቸው ተገፎ እርቃናቸውን ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አሳየ።
በቢቢሲ ትክክለኛነቱ በተረጋገጠው ቪዲዮ ላይ መላ ልብሳቸው ወልቆ ራቁታቸውን በውስጥ ሱሪ ብቻ ሆነው በእስራኤል ወታደሮች የሚጠበቁ ወንዶች መሬት ተንበረክከው ይሳያል።
የእስራኤል ጦር ኻን ዩኒስ በተሰኘችው ከተማ እና በሰሜናዊ ጋዛ አካባቢዎች ከሐማስ ጋር ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እና ጦርነት እያካሄደ ነው።
በቪዲዮው ላይ የታዩት ወንዶች ከጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ አቅጣጫ ላይ በምትገኘው ቤይት ላህያ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ተነግሯል።
በእስራኤል ወታደሮች እንዲህ ባለው ሁኔታ ከተያዙት ፍልስጤማውያን መካከል ታዋቂ ጋዜጠኛ የሚገኝበት ሲሆን፣ ቀጣሪዎቹም እስራኤል “መብት የሚጥስ እና አዋራጅ የሆነ አያያዝን” በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየፈጸመች ነው በማለት ከሷል።
ቪዲዮውን በተመለከተ የተጠየቁት የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት ወንዶች በወታደርነት ለመሰማራት በሚያስችል እድሜ ላይ ያሉ እና “ነዋሪዎች ከሳምንታት በፊት ለቀው እንዲወጡ በታዘዙባቸው አካባቢዎች የተገኙ ናቸው” ብለዋል።
ቪዲዮው ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶች በዙሪያቸው ተበታተነው የሚታዩ ልብሳቸውን እና ጫማቸውን አውልቀው በአንድ ጎዳና ጥግ ላይ ተሰልፈው ይታያሉ። በዙሪያቸውም የእስራኤል ወታደሮች እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል።
በአንድ ምስል ላይ ደግሞ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች በወታደራዊ ካሚዮን ላይ ተጭነው ሲወሰዱ ታይተዋል። የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ደግሞ፣ የተያዙት ፍልስጤማውያንን እጅ የሰጡ የሐማስ ተዋጊዎች ናቸው ብለው ገልጸዋቸዋል።
ሌላ አስካሁን ትክክለኛነቱ በቢቢሲ ያልተረጋገጠ ምስልም እንዲሁ የተያዙት ሰዎች ዐይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ፣ በቡልዶዘር የተቆፈረ በሚመስል ጉድጓድ መሳይ አሸዋማ ቦታ ላይ ተንበርክከው አሳይቷል።
- “በጋዛ ሕይወት እየጨለመብኝ ነው” – በጋዛ ያለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ8 ታህሳስ 2023
- ጋዛ፡ “የት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት? እንዲህ ሆነን የት እንሂድላቸው?”7 ታህሳስ 2023
- እስራኤል የሐማስን ዋሻዎች ከባሕር በሚሳብ ውሃ በማጥለቅለቅ ልታወድም ነው6 ታህሳስ 2023
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባይሰጥም፣ ቃል አቀባዩ ዳንኤል ሃጋሪ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ “የእስራኤል ጦር ኃይል አባላት እና የሺን ቤት መኮንኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሽብር ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ አካሂደዋል” ብለዋል።
“ባለፉት 24 ሰዓታት በርካቶች እጃቸውን ሰጥተዋል። ከምርመራው የሚገኘውን መረጃ ጦርነቱን ለማስቀጠል የምንጠቀምበት ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ኤይሎን ሌቪይ ዛሬ አርብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ፍልስጤማውያኑ የተያዙት “የሐማስ ጠንካራ ይዞታ እና የትኩረት ማዕከል ከሆኑት” በሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኙት ጃባሊያ እና ሼጃይያ ነው ብለዋል።
ጨምረውም “እየተናገርን ያለው ለሲቪሎች ከሳምንታት በፊት ለቀው መውጣት ካለባቸው አካባቢዎች የተገኙ እና በወታደራዊ አገልግሎት ሊሰለፉ ስለሚችሉ ወንዶች ነው” በማለት በተያዙት ሰዎች ላይ በሚደረገውም ምርመራ “ማን የሐማስ አሸባሪ እንደሆነ እና እንዳልሆነ ይለያል” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም ሰዎች የተያዙት የእስራኤል ኃይሎች ከሐማስ ጋር “በቅርብ ርቀት ውጊያ” ባካሄዱበት አካባቢ መሆኑን ገልጸው፣ ከሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ሕንጻዎች በመነሳት “ሲልች ለመምሰል” ሲሞክሩ ነበር ብለዋል።
በእስራኤል ሠራዊት ሐሙስ ዕለት ቤይት ላሂያ ውስጥ ከተያዙት ሰዎች መካከል 10 የቅርብ ዘመዶቹ እንደሚገኙበት አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ግለሰቡ ለቢቢሲ የአረብኛ አገልግሎት እንደተናገረው፣ የእስራኤል ወታደሮች ወደ አካባቢው በመግባት በድምጽ ማጉያ በቤታቸው እና በተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅት ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ ወንዶች እንዲወጡ አዘዋል።
ጨምሮም ወታደሮቹ በአካባቢው ያሉ ሴቶች በአቅርቢያ ወደ ሚገኘው ሆስፒታል እንዲሄዱ ካዘዙ በኋላ፣ ወንዶቹ ከቤታቸው የማይወጡ ከሆነ እንደሚተኩሱባቸው እንዳስፈራሯቸው ገልጿል።
ግለሰቡ ከ10ሩ ዘመዶቹ መካከል ሰባቱ ተለቀው ወደ ቤታቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ነገር ግን በእስራኤል ወታደሮች ተይቀዘው የቀሩት የቀሪዎቹ ሦስት ዘመዶቹ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ እንደማያውቅ ተናግሯል።
በዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም አምባሳደር በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ይፋ የሆነውን ቪዲዮ “ሲቪሎች ከተባበሩት መንግሥታት መጠለያ ተወስደው ራቁታቸውን እንዲሆኑ የተደረገበት ክስተት የእስራኤል የጭካኔ ወረራ ምስል ነው” ሲሉ ቪዲዮውን ገልጸውታል።
የ’አል-አራቢ አል-ጃዲድ’ ጋዜጠኛ የሆነው ታዋቂው ፍልስጤማዊ ዲያነ አል-ኻሉት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል መሆኑም ተረጋግጧል።
ከአረብኛ በዘለለ ‘ዘ ኒው አራብ’ በተሰኘ ስም በአንግሊዝኛ ቋንቋም ዘገባ የሚሠራው መገናኛ ብዙኃን፤ አል-ኻሉት ከወንድሞቹ እና ዘመድ አዝማዶቹ እንዲሁም “ከሌሎች ሰላማዊ ሰዎች” ጋር ቤይት ላህያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ አሳውቋል።
አል-አራቢ አል-ጃዴድ “ሐሙስ ዕለት አል-ኻሉት ክብርን በሚገፍ መልኩ በቁጥጥር ሥር መዋሉን” በፅኑ እንደሚኮንነው ገልጧል።
የመገናኛ ብዙኃኑ አክሎም ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸውን ወንዶች ልብስ በግድ አውልቀው “ባልተገባ ሁኔታ ሲፈትሿቸው እና ክብራቸውን በሚነካ መልኩ ሲያንገላቷቸው ቆይተው በመኪና ጭነው ወዳልታወቀ ሥፍራ ወስደዋቸዋል” ብሏል።
አል-አራቢ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፤ የጋዜጠኞች መበት ተከራካሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተካሄደ ያለውን ጥቃት ሊያወግዙት ይገባል” ሲል እስራኤል እየፈፀመችው ያለችውን አንድ እንዲሉ ጥሪ አቅርቧል።
ቢቢሲ፤ የእስራኤል መከላከይ ሠራዊት ስለ አል-ኻሉት ሁኔታ አስተያየት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል።