December 8, 2023 

አፍሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ የምግብ ዋስትና እጦት ችግር መጠቃቷ ተገለፀ።

አፍሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የምግብ ዋስትና እጦት ችግር እንደገጠማት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲገልፅ ወደ 75 በመቶ አፍሪካውያን ለጤና ተስማሚ የሆኑ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ምግቦችን ለማግኘት የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው ገልጿል።

በተጨማሪም 20 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው ሪፖርቱ ያመለከተ ሲሆን  የአህጉሪቱ 1.4 ቢሊዮን ህዝብ ለከፍተኛ ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር ላይ መሆኑን አመላክቷል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የአለም እህል አቅርቦት ላይ ጉዳት ማድረሱ ሲገለፅ የአፍሪካ ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የ COVID-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ውጤት ማምጣቱን ተከትሎ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ዜጎች የረሃብ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል በማለት የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።

በአህጉሪቱ በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ የተቃጡ ጥቃቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል የተባለ ሲሆን  በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ በአርሶ አደሮች  ላይ ከፍተኛ ስጋት በመፍጠሩ የዜጎች ገቢና የምግብ ዋጋ ሊመጣጠን አለመቻሉ ተጠቅሷል።

እ.ኤ.አ. በ 2022 እስከ 342 ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪካውያን በከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ችግር የተጠቁ መሆኑ ሲገለፅ ይህም በዓለም ዙሪያ ካሉ 735 ሚሊዮን ምግብ ያጡ ሰዎች መካከል 38 በመቶውን የሚወክል መሆኑን የምግብ እና ግብርና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአለም የምግብ ፕሮግራም እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሪፖርት አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ አፍሪካ እየጣለ ያለው ቀባድ ዝናብ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ሲጠቀስ የአየር ንብረት ለውጥ መባባሱን የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች ቡድን አስታውቋል።

በጥቅምት እና ህዳር መካከል ባለው ወቅት የጣለው የዝናብ መጠን ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተመዘገበው የበለጠ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።

በአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የዝናቡ መጠን በእጥፍ መጨመሩን ተመራማሪዎቹ ሲያሳውቁ በቀጠናው በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጎድተው ከ 1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከመኖሪያቸው ተፈናቀቅለዋል ተብሏል።

ሶማሊያ ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ ዋና ተጠቂ መሆናቸው ሲገለፅ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲና ዩጋንዳ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሀገራት መሆናቸው ተጠቅሷል። ዝናቡ እስከ ፈረንጆቹ 2024 መጀመሪያ ድረስ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።