
9 ታህሳስ 2023, 08:08 EAT
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን በመጪው መጋቢት ወር በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።
ፑቲን ከሦስት ወር ገደማ በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ይፋ ያደረጉት በዩክሬን ጦርነት ተሳታፊ ለሆኑ ወታደሮች ሽልማት በሰጡበት መድረክ ላይ ነው።
የአገሪቱ ምርጫ አስፈጻሚ ኃላፊዎች ቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመጋቢት 6 እስከ 8/2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ይፋ አድርገዋል።
ይህ ነው የሚባል ተቀናቃኝ በሌለበት ሩሲያን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡት የ71 ዓመቱ ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ መመረጣቸው አይቀሬ ነው።
ፑቲን ከአውሮፓውያኑ ከ2000 – 2008 ድረስ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።
ከ2008 እስከ 2012 ደግሞ በቅርብ ወዳጃቸው ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የፕሬዝዳንትነት አስተዳደር ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ እአአ 2012 ላይ ተመልሰው የፕሬዝዳንት መንበሩን በመያዝ አገሪቱን አሁን ድረስ በጠንካራ ክንዳቸው እየመሩ ይገኛሉ።
ፑቲን ከቸውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት እየሆኑ ለረዥም ጊዜ ሶቪየት ኅብረትን ከመሩት ጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል ኃያሏን አገር የስተዳደሩ በታሪክ ሁለተኛው ሰው ሆነዋል።
- የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ፑቲን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ተጓዙ7 ታህሳስ 2023
- ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ የደኅንነት ቢሮ ለዓመታት መረጃ ሲመዘብረኝ ቆይቷል አለች7 ታህሳስ 2023
- ፑቲን የሩሲያ ጦር ሠራዊት አባላት ቁጥርን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለማሳደግ ወሰኑ2 ታህሳስ 2023
የሩሲያ ሕገ-መንግሥት እአአ 2020 ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ከአራት ወደ ስድስት ዓመት ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ፑቲን ያልተጠበቀ ነገር አስካልተፈጠረ ድረስ ያሸንፉበታል በሚባለው መጋቢት ላይ የሚካሄደው ምርጫ የሥልጣን ዘመናቸው እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ ያስቀጥለዋል።
ከዚያ በኋላም ቢሆን ፑቲን በሥልጣን የመቆየት ፍላጎት የሚኖራቸው ከሆነ እስከ 2036 በመሪነት መንበር ላይ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ።
የሶቪየት ኅብረት የስለላ መሥሪያ ቤት ውስጥ መኮንን የነበሩት፤ የአሁኑ ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦራቸውን ዩክሬን ላይ ማዝመታቸው ያመጣባቸውን መዘዝ ተከትሎ በቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊሳተፉ እንደሚችሉ በስፋት የተጠበቀ ነበር።
ፑቲን እውነተኛ ተቃዋሚዎቻቸው በሕይወት የሌሉ፣ በእስር ላይ ያሉ አሊያም ከአገር ወጪ በመሆናቸው በቀጣይ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ተቀናቃኝ እንደሌላባቸውም ግልጽ ነው።
ሐሙስ ዕለት የሩሲያ ምክር ቤት ምርጫው እንደሚካሄድ ይፋ ካደረገ እና የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ምርጫ የሚካሄድባቸውን ቀናት ካሳወቀ በኋላ፣ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ፑቲን በመሪነት እንዲቀጥሉ ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ቢሆኑ በሥልጣን የመቆየት ፍላጎት እንዳላቸው ለመግለጽ ጊዜ አልወሰደባቸውም።
ፕሬዝዳንቱ በዩክሬን ጦርነት ለተሳተፉ ወታደሮች የሩሲያን ጀግና ሜዳሊያ በሰጡበት ሥነ ሥርዓት ላይ “ውሳኔ መሰጠት ያለበት ጊዜው አሁን ነው። ለሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት እወዳደራለሁ” ብለዋል በአገሪቱ ቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው።
ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ የሥልጣን መንበር የመጡት እአአ 1999 ላይ በጤና መቃወስ ይሰቃዩ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ቦሪስ ዬልሲንን በመተካት እንደነበረ ይታወሳል።
ፑቲን ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ መንበራቸውን በማደላደል በሩሲያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ ሲያጠናክሩ ቆይተዋል።