ጋዛ ውስጥ ካሉ ቡድኖች መካከል ሐማስ ኃያሉ ነው
የምስሉ መግለጫ,ጋዛ ውስጥ ካሉ ቡድኖች መካከል ሐማስ ኃያሉ ነው

9 ታህሳስ 2023

በቅርቡ የሐማስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሙሳ አቡ ማርዙክ በጋዛ ያሉ ሁሉም ታጋቾች በሐማስ ቁጥጥር ስር እንደማይገኙ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አመራሩ በቃለ መጠይቁ አንዳንድ ታጋቾች በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ በሆኑ “በተለያዩ አንጃዎች” ተይዘው እንደሚኙ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በዚያ ጥቃት ከሐማስ ጎን ተሰልፈው ተሳታፊ የሆኑ አምስት ቡድኖችን ለይቶ ነበር።

ምንም እንኳን እነዚህ ቡድኖች በእስራኤል ላይ የኃይል ጥቃት በመሰንዘር ላይ ተመሳሳይ አቋም ቢኖራቸውም፣ የወደፊቷ ነጻ ፍልስጤም ስለምትመራበት አግባብ እና ሃይማኖት የሚኖረውን ሚና በተመለከተ የተለያየ አቋም ነው ያለቸው።

በጋዛ ምን ያህል ታጣቂ ቡድኖች እንዳሉ በትክክል ባይታወቅም ስለተወሰኑት የሚታወቁ እውነታዎች አሉ።

የሐማስ ተዋጊዎች ከእስራኤል ያገቷቸውን ለቀይ መስቀል ካስረከቡ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ (ኅዳር 29/2016 ዓ.ም.)
የምስሉ መግለጫ,የሐማስ ተዋጊዎች ከእስራኤል ያገቷቸውን ለቀይ መስቀል ካስረከቡ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ (ኅዳር 29/2016 ዓ.ም.)

ሐማስ/ አል-ቃስም ብርጌድ

በሙሉ መጠሪያው ኢዛ አል-ዲን አል-ቃሳም ብርጌድ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ሲሆን፣ ከእአአ 2007 ጀምሮ በጋዛ አስተዳዳሪነት ላይ ይገኛል።

የጦር ክንፉ መጠሪያውን ያገኘው የፍልስጤማውያን የነጻነት ታጋይ ተድርገው ከሚታዩት የሃይማኖት መሪ ነው።

ይህ ቡድን ከእስራኤል ጋር በበርካታ ጦርነቶች ተፋልሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል፤ በአጥፍቶ ጠፊ ወታደሮቹ እስራኤልን አጥቅቷል።

ሐማስ መሠረቱ ከግብፁ የሙስሊም ወንድማማችነት እንቅስቃሴ ነው። የሙስሊም ወንድማማችነት እአአ 1920ዎቹ እስላማዊ አስምህሮዎችን እና ሞራሎችን ለማስፋፋት በሚል እንቅስቃሴ ቢጀምርም በሂደት ፖለቲካዊ ሚናዎችን መጫወት ጀመረ።

ከሙስሊም ወንድማማችነት ዓላማዎች መካከል አንዱ በእስላማዊ ሕግጋት ወይም በሸሪዓ የሚተዳደር አገር እውን ማድረግ ነው።

እአአ 2017 ላይ ሐማስ ከሙስሊም ወንድማማችነት ጋር ያለኝ ግንኑነት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ብሎ ይፋ አድርጎ ነበር። የቢቢሲ አረብኛ ባልደረባ ፌራስ ኪላኒ ግን ይህ እውነት አለመሆኑን እና የእንቅስቃሴው እና የሐማስ ግንኙነት ከመጋረጃ ጀርባ እንደቀጠለ ያምናል።

በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በሌሎች ምዕራባውያን አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሐማስ፤ ወታደራዊ ክንፉ እስራኤል ላይ መስከረም 26 የተቃጣውን ድንገተኛ ጥቃት መርቷል።

ሐማስ በጋዛ ሰርጥ ከ20 አስከ 30 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ይታመናል።

ኢራን ዋነኛ የሐማስ ድጋፍ ሰጪ ነች። ሐማስ ገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ እና ሥልጠና ከኢራን ያገኛል። የሐማስ መሪዎችም በተለያዩ አጋጣሚዎች በይፋ ኢራንን ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ካርታ

የፍስልጤም እስላማዊ ጂሃድ /አል-ቁዱስ ብርጌድ

አል-ቁዱስ ብርጌድ ከአል-ቃስም ብርጌድ በመቀጠል በጋዛ ጠንካራው ወታደራዊ ኃይል እንደሆነ ይተመናል።

ይህ ቡድን እአአ በ1980ዎቹ የእስላማዊ ጂሃድ እንቅስቃሴ ወታደራዊ ክንፍ ሆኖ ነበር የተቋቋመው። ልክ እንደ አብዛኞቹ ቡድኖች ሁሉ ይህ ቡድንም በምዕራባውያን መንግሥታት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ተፈርጇል።

መጠሪያው በአረብኛ ቋንቋ ኢየሩሳሌም የሚል ትርጓሜ ያለው ይህ ቡድን ዝናን ያተረፈው እአአ 2002 ላይ ከእስራኤል ጦር ጋር በዌስት ባንክ ጠንካራ ውጊያ ካደረገ በኋላ ነው።

ቡድኑ እስከ 2ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች እንዳሉት ይታመናል። ከኢራን ጋር ያለው ግንኙነት ከሐማስ በላይ ጠንካራ እንደሆነ ይነገራል።

የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድም (ፒአይጄ) ሆነ ሐማስ ሃይማኖት ዋነኛ ሚና የሚኖርባት ነጻ ፍልስጤም እንድትመሠረት ፍላጎት ቢኖራቸው ልዩነቱ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ጠንካራ ሃይማኖታዊ አገር እንድትሆን መፈለጉ ነው።

በቅርቡ የዚህ ቡድን ከፍተኛ አመራር ከአል ጃዚራ አረብኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቡድኑ በመስከረም 26ቱ ጥቃት 30 ሰዎችን አግቶ መውሰዱን የተናገሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ተይዘው የነበሩት ሴቶች እና ሕጻናት በቅርቡ ከተለቀቁት መካከል ይገኙበታል ብለዋል።

ይህ የፒአይጄ ከፍተኛ አመራር በአሁኑ ወቅት በቡድኑ ስንት ሰዎች ተይዘው እንደሚገኙ ከመናገር ተቆጥበዋል።

የፍልስጤም እስላሚዊ ጂሃድ አባላት በእስራኤል የተገደሉ ፍልስጤማውያንን ለማሰብ ተሰብስበው (ሰኔ 2015 ዓ.ም.)
የምስሉ መግለጫ,የፍልስጤም እስላሚዊ ጂሃድ አባላት

የፍልስጤም ነጻነት ሕዝባዊ ግንባር/ አቡ አሊ ሙስታፋ ብርጌድ

ከዚህ ቀደም ፖፑላር ሬዚዝስታንስ ፎርስ (ሕዝባዊ የነጻነት ኃይል) ተብሎ ይጠራ የነበረው አቡ አሊ ሙስታፋ ብርጌድ የማርክሲስት-ሌኒኒስት ወይም የኮሚኒስት ቡድን የሆነው የፒኤፍኤልፒ የጦር ክንፍ ነው።

ይህ ቡድን ከፍተኛ እውቅናን ያገኘው እአአ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ አውሮፕላኖችን በጥለፍ እና በመላው ዓለም ጥቃቶችን በመፈጸም ነው።

ከሐማስ መምጣት በፊት ሁለተኛው ትልቁ የፍልስጤም ቡድን ነበር።

አንዳንድ ሪፖርቶች ይህ ቡድንም ታጋቾችን ይዞ እንደሚገኝ ቢጠቁሙም ቢቢሲ ግን ይህን በራሱ ወይም ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

አል-ናሲር ሳላህ አል-ዲን ብርጌድ

የተመሠረተው እአአ በ2000 ነው። አንዳንድ ሪፖርቶች ይህ ቡድን ከሐማስ ጋር በመተባበር እአአ 2006 ላይ ጊላድ ሻሊት የተባለ የእስራኤል ወታደር እገታ ላይ ስለመሳተፉ ያመለክታሉ።

ቡድኑ በተዋጊዎች ብዛት በጋዛ ሦስተኛው ትልቁ አንጃ ሲሆን፣ የሐማስ እና ፒአይጄ አጋር ነው። ለጋዛ የፖሊስ ኃይልም የሰው ኃይል ያዋጣል።

አል-ናሲር ሳላህ አል-ዲን ብርጌድ በራሱ አቅም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ የሚችል ሲሆን፣ በመስከረም 26ቱ ጥቃት ወቅትም በርካታ የእስራኤል ወታደሮችን አግቻለሁ ቢልም ለዚህ ግን ምንም ማረጋገጫ አልሰጠም።

እአአ 2015 ላይ የሙጃሃዲን አባላት የቡድኑን 14ኛ ዓመት ምስሠረታ በማስመልከት በጋዛ ጎዳናዎች በወጡ ወቅት።
የምስሉ መግለጫ,የሙጃሂዲን ብርጌድ አባላት

ሙጃሂዲን ብርጌድ

ይህም መሠረቱ ከፋታህ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፤ ከእስላማዊ ጂሃድ እና ጽንፈኛ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው።

ይህ ቡድንም እንዲሁ በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳትፎ አድርጎ ታጋቾችን ይዞ እንደሚገኝ ይገልጻል።

የአል-አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ

ይህ ቡድን በፋታህ እውቅና ባይሰጠውም በያሲር አራፋታ እና በሌሎች ከተመሠረተው ፋታህ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል።

ፋታህ ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት የጸዳ ዌስት ባንክን እያስተዳደረ ያለ ፓርቲ ነው።

ፋታህ እአአ 2006 ላይ በጋዛ በተደረገ ምርጫ በሐማስ ከተሸነፈ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ከጋዛ ሰርጥ በሐማስ በኃይል ተገፍቶ እንዲወጣ ተደርጓል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ባደረገው ምርመራ አንዳንድ የአል-አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባላት በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ መሆናቸውን አሳይቷል።

ቢቢሲ እጅ የገቡ ምስሎች የቡድኑ አባላት ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት እና ከዚያ በፊት በነበሩ ቀናት ከሌሎች ቡድኖች ጋር ልምምድ ሲያደርጉ ያሳያሉ።

የቢቢሲው ዘጋቢ በጥቃቱ የመሳተፍ ውሳኔ የቡድኑ ይሁን፣ አባላቱ በግለሰብ ደረጃ ባሳለፉት ውሳኔ ማወቅ እጅጉን ከባድ ነው ይላል።