ነጭ ሽንኩርት

9 ታህሳስ 2023, 10:38 EAT

አንድ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል አገራቸው ከቻይና የምታስገባው ነጭ ሽንኩርት በአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በመሆኑ የሚያስከትለው ተጽእኖ እንዲመረመር ጥሪ አቀረቡ።

የሪፐብሊካን ፓርቲው ተወካይ እንደራሴ ሪክ ስኮት ለአሜሪካ መንግሥት ንግድ መሥሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ ላይ፣ ከቻይና የሚመጣው ነጭ ሽንኩርት ንጽህናው በተጠበቀ ሂደት ያልተመረተ መሆኑን በማመልከት ጉዳትን ያስከትላል ብለዋል።

ቻይና በዓለም ላይ ነጭ ሽንኩርት ወደ ተላየዩ አገራት በመላክ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ አሜሪካ ደግሞ ዋነኛዋ የምርቱ ተጠቃሚ ናት።

ነገር ግን በሁለቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የነበረው የነጭ ሽንኩርት ንግድ ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ የቆየ ነው።

ለዚህም ምክንያቱ ቻይና የነጭ ሽንኩርት ምርቷን ከሚገባው በታች በሆነ ዋጋ እያቀረበች ገበያዋን “አጥለቅልቃለች” በማለት አሜሪካ መክሰሷ ነው።

ከአውሮያኑ 1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶም በርካሽ ዋጋ ከሚቀርቡ የቻይና ምርቶች የአሜሪካን አምራቾች ለመጠበቅ በሚል አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ ቀረጥ ወይም ታሪፍ ጥላለች።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ደግሞ በምርቶቹ ላይ የተጣለው ታሪፍ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

የምክር ቤት አባሉ ስኮት ከቻይና በሚገባው ነጭ ሽንኩርት ላይ ያላቸውን ስጋት በገለጹበት ደብዳቤያቸው ላይ “በውጭ አገራት በተለይም ደግሞ በኮሚኒስት ቻይና በሚመረተው ነጭ ሽንኩርት ጥራት እና ደኅንነት ላይ አሳሳቢ የጤና ስጋት አለ” ብለዋል።

ለዚህ ክሳቸውም በቆሻሻ ፍሳሽ መስመሮች ላይ ነጭ ሽንኩርት ማብቀል ጨምሮ “በመረጃ የተረጋገጡ” ያሏቸውን በይነ መረብ ላይ ያሉ ቪዲዮዎችን፣ የምግብ ማብሰል ፕሮግራሞችን እና ዶክምንታሪዎችን በማስረጃነት ጠቅሰዋል።

የምክር ቤት አባሉ በአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ተጽእኖ ባላቸው ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ምርመራ እንዲደረግ በሚፈቅደው የአገሪቱ ሕግ መሠረት በቻይና የነጭ ሽንኩርት ምርት ላይ የንግድ መሥሪያ ቤቱ ምርመራ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ስኮት በሚደረገው ምርመራ ከቻይና ገብተው በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሁኔታዎች ተዘጋጅተው በሚገኙት የነጭ ሽንኩርት ምርቶች ላይ አጠቃላይ ምርመራ እንዲደረግ በዝርዝር ጠይቀዋል።

ጨምረውም “የምግብ ጤናማነት እና ደኅንነት ጉዳይ በአገራችን ብሔራዊ ደኅንነት፣ በሕብረተሰብ ጤና እና በምጣኔ ሃብት ብልጽግና ላይ ተጨባጭ ስጋትን የሚደቅን ነው” ብለዋል።

በሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያቀርበው ካናዳ ኪዩቤክ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የሳይንቲፊክ ሶሳይቲ እንዳለው በቻይና ውስጥ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽን እንደማዳበሪያነት በመጠቀም ነጭ ሽንኩርት ይበቅላል መባሉን የሚያረጋግጥ “ምንም ማስረጃ የለም” ብሏል።

ይህም ቢሆን ችግር እንደሌለው ከስድስት ዓመት በፊት ባወጣው ጥናት ላይ “የሰው ዐይነ ምድር እንደ እንስሳቱ ሁሉ ለማዳበሪያነት ቢውል ውጤታማ ነው። በእርሻ ቦታ ላይ ዐይነ ምድርን መጠቀም ደስ የሚል ባይሆንም፣ እንደሚታሰበው ግን ችግር አያማጣም” ሲል ገልጿል።