
9 ታህሳስ 2023, 09:36 EAT
የእስራኤል ወታደሮች አንድ ታጋችን ለማስለቀቅ ጋዛ ውስጥ ባካሄዱት ባልተሳካ ወታደራዊ ዘመቻ ታጋቹ መገደሉን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ገለጸ።
ወታደራዊ ቡድኑ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ባልተሳካው የእስራኤል ታጋች የማስለቀቅ እርምጃ በደረሰ ጉዳት አንድ ታጋች መገደሉን አመልክቷል።
በምሥሉ ላይ አንድ ታጋች በዚያ ስፍራ ለ40 ቀናት መያዙን ሲናገር የሚሰማ ሲሆን፣ ይህም ቪዲዮ የተቀረጸው በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።
ቪዲዮው ጨምሮም በርካታ ደም የፈሰሰበት ወለል እና ሐማስ ከእስራኤል ወታደሮች የማረኳቸው ናቸው ያላቸው ወታደራዊ ትጥቆችን አሳይቷል።
ቪዲዮው የሚያበቃው ቀደም ሲል ከአንድ ወር በላይ ታግቶ መቆየቱን ሲናገር የነበረው ግለሰብ በደም የተሸፈነ አስቃቂ አስከሬንን በማሳየት ነው።
በቪዲዮው ላይ ድምጹ የሚሰማው የሐማስ አባል የሟቹን ግለሰብ ስም እና ዕድሜን የሚናገር ቢሆንም፣ ቢቢሲ እነዚህ የግለሰቡን ማንነት ገላጭ የሆኑ ዝርዝሮችን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
በቪዲዮው ላይ በአረብኛ የተጻፈ ጽሁፍ የእስራኤል ወታደሮች ታጋቹ ጋር “ሳይደርሱ ቀርተዋል” በማለት፣ በዚህም ምክንያት ለታጋቹ ሞት ሰበብ መሆናቸውን በመግለጽ ከክስተቱ በኋላ ወታደሮቹ “በፍጥነት ቦታውን ለቀው ሸሽተዋል” ብሏል።
- እስራኤል የሐማስን ዋሻዎች ከባሕር በሚሳብ ውሃ በማጥለቅለቅ ልታወድም ነው6 ታህሳስ 2023
- “በጋዛ ሕይወት እየጨለመብኝ ነው” – በጋዛ ያለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ8 ታህሳስ 2023
- በጋዛ ከሐማስ ሌላ ስንት የፍልስጤማውያን ታጣቂ ቡድኖች አሉ? እነማንስ ናቸው?9 ታህሳስ 2023
በተጨማሪም የእስራኤል ወታደሮች ታጋቹ ወደ ተያዘበት ስፍራ ለመድረስ አምቡላንስ መጠቀማቸውን በመጥቀስ ከሷል።
ቢቢሲ በሐማስ የተለቀቀውን ቪዲዮ ትክክለኝነትን ማጣራት ያልቻለ ሲሆን፣ በሐማስ ለተባሉት ነገሮች ከሌሎች ወገኖች ማረጋገጫ አላገኘም።
ትናንት አርብ ምሽት በተሰጠ መግለጫ ላይ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ፣ ጋዛ ውስጥ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በተካሄደ ዘመቻ ወቅት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ክፉኛ መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።
እንዲሁም “ታጋቾችን በመጥለፍ እና ይዞ በማቆየት የተሳተፉ ሽብርተኞች” መገደላቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን የታገቱ ሰዎችን እንዳላስለቀቁ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በመግለጫው ላይ ማብራሪያ የተሰጠበት ሁኔታ ሐማስ ካሰራጨው ቪዲዮ ጋር በተያያዘ ክስተት ያጋጠመ ይሁን ወይም ሌላ ግልጽ አይደለም።
የእስራኤል ጦር ኃይል በጋዛ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ የጀመረው የሐማስ ተዋጊዎች በመስከረም ወር ማብቂያ ላይ ወደ አስራኤል ዘልቀው በመግባት ከባድ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።
በዚህ ጥቃትም 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 240 የሚሆኑ ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን አስራኤል አስታውቃለች።
ከሳምንት በፊት በተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ጥቂት የማይባሉ ታጋቾች ቢለቀቁም፣ ሐማስ ከእስራኤል ጦር ሠራዊት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸው ታጋቾች አሁንም በቁጥጥሩ ስር ናቸው።
እስራኤል ጋዛ ውስጥ እያካሄደችው ባለው ዘመቻ በቀዳሚነት ታጋቾችን ማስለቀቅ እና ሐማስን ከግዛቲቱ ማስወገድ ዓላማዋ መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
በጋዛ ላይ እያስፋፋችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻም አስካሁን ድረስ ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ሲያስታውቅ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በከባድ ችግር ላይ መሆናቸው ይነገራል።