በአሪ ዞን ቶልታ ከተማ ተከስቶ የነበረ ግጭት እርቅ ስርአት ሲከናወን

9 ታህሳስ 2023

በመላው አገሪቱ የሚከበረው የኢትዮጵያ ይፋዊ አዲስ ዓመት መስከረም 1/2016 ዓ.ም. ተጀምሮ ሦስተኛ ወሩን አገባዷል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የራሳቸው የሆነ የአዲስ ዓመት አከባበር እና ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶች አሏቸው።

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የመስከረም ወር የዓመቱ መጀመሪያ ሲሆን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት አሪዎች ደግሞ መስከረም ወይንም ታማ 10ኛ ወራቸው ነው።

እነርሱ በአራተኛው ወር በታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. አዲስ ዓመታቸውን አንድ ብለው ይጀምራሉ።

ለአሪዎች የዓመቱ መጀመሪያ ወር ሎንጋ ይሰኛል፤ ታኅሣሥ እንደ ማለት ነው። አቆጣጠሩ የጨረቃን ዑደት የተከተለ ነው።

የአሪ የአገር ሽማግሌው አቶ ዳኜ ገብሬ እንዲሁም የዞኑ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ ታምራት፣ አሪዎች 12 ወራት ብቻ እንዳሏቸው ይናገራሉ።

የአሪ ብሔረሰብ ቀን የሚቆጥረው ጨረቃ ከታየችበት ዕለት ጀምሮ እስክትጠልቅ ያለው ዕለት በመሆኑ በይፋዊው የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ ላይ የምትገኘው13ኛዋ ወር ጳጉሜ ስሌት ውስጥ አትገባም።

አቶ ታምራት ተስፋዬ የአሪ ዞን የመንግሥት ኮሙኑኬሽን መምሪያ ኃላፊ “ድሽታ ግና” [አዲስ ዓመት]፣ አስቸጋሪው የክረምት ወቅት አልፎ፣ የተዘራው እህል ደርሶ ጎረቤት እና ቤተዘመድ ተጠራርቶ የሚበላበት፣ ባቢዎችና ጎድሚዎች (ባላባቶች እና የባህል ሥርዓት መሪዎች) እህል ቀምሰው ከስር ላለው ማኅበረሰብ (ከይስዎች) የሚያደርሱበት በዓል ነው ይላሉ።

ለአገር ሽማግሌው አቶ ዳኜም ያለው ለሌለው አካፍሎ የሚበላበት የአሪዎች አዲስ ዓመት ድሽታ ግና ነው።

ድሽታ ግና ምን ማለት ነው?

የአሪ ብሔረሰብ ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ ደቡብ ኦሞ በሚባለው ዞን ውስጥ ነበር የሚገኘው።

አሁን ደግሞ አዲስ በተዋቀረው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር ተደራጅቷል።

በአሪ ዞን ውስጥ አራት ወረዳ እና ሁለት የከተማ አስተዳደር አለ።

አራቱ ወረዳዎች ሰሜን አሪ፣ ዎባ አሪ፣ ደቡብ አሪ፣ ባካ ደውላ የሚባሉ ሲሆን፣ ጂንካ እና ገሊላ ከተማ ደግሞ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው።

በዓመቱ መጀመሪያ ወር፣ መጀመሪያ ቀን በክብረ በዓል የሚደምቀው የዕለት መጠሪያው ‘ድሽታ ግና’ ከሁለት ጥምር ቃል የተመሠረተ ነው።

ድሽታ የሚለው ከደቡብ አሪ ሲወሰድ፣ ግና ደግሞ ከሰሜን አሪ የተገኘ መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጆች አቶ ታምራት እና አቶ ዳኜ ያስረዳሉ።

“ድሽታ የሚለው ቃል በርካታ ትርጉሞች አሉት። የመጀመሪያው የተጣደ ማለት ነው። ግና ደግሞ የበሰለ ማለት ነው። ስለዚህ ተጥዶ የበሰለ የሚል ትርጉም ይሠጣል” የሚሉት አቶ ታምራት ናቸው።

አቶ ዳኜ በበኩላቸው ድሽታ በደቡብ አሪ ምስጋና፣ ደስታ ማለትም ይሆናል ይላሉ። ግና ደግሞ የሰሜን አሪ ዘዬ ነው። በጋራ የምስጋና በዓል የሚለውን ይሰጣል ሲሉ ያስረዳሉ።

አሪዎች አሮጌውን ዓመት አሰናብተው አዲሱን ዓመት ሊቀበሉ ነው።

የአሪ የዘመን አቆጣጠር 12ቱ ወሮች ብቻ ያሉት መባቻውም በታኅሣሥ ወር (ሎንጋ) የመጨረሻው ወር ደግሞ ኅዳር (ሶምዛ) እንደሚሰኝ የብሔረሰቡ አባላት ይናገራሉ።

የወራቱ ስሞች በአሪ አፍ እና በአማርኛ በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ይገልጿቸዋል።

ሎንጋ – ታኅሣሥ፣ ቶራ – ጥር፣ ማከን – የካቲት፣ ኦይዲ – መጋቢት፣ ዶላ – ሚያዝያ፣ ላ – ግንቦት፣ ታብዛ – ሰኔ፣ ዜታ – ሐምሌ፣ ሳግላ – ነሐሴ፣ ታማ – መስከረም፣ በክሳ – ጥቅምት፣ ሶምዛ – ኅዳር ናቸው።

በአሪ ብሔረሰብ የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ዳኜ ገብሬ፣ የድሽታ ግናን በዓል ለማክበር ከወርሃ ኅዳር ጀምሮ በቤተሰብ እና በግለሠብ ደረጃ ዝግጅት ይደረጋል ይላሉ።

በዓሉ ያለፈውን ዘመን የተፈጠሩ ቁርሾዎች እና ቂሞችን በማስወገድ አዲሱን ዘመን በሰላም እና በተስፋ ለመቀበል የሚደረግ በመሆኑ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበር ነው።

አቶ ታምራት በበኩላቸው አሪዎች ከኅዳር ወር ጀምሮ ተጣልተው እና ተኳርፈው የድሽታ ግናን በዓል በምንም ዓይነት ሁኔታ አያከብሩም ይላሉ።

ባሕላዊ ሥርዓቱ እንዲታረቁ ያስገድዳል። ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ የተጣላም ይታረቃል፣ እንደ ማኅበረሰብም በቡድኖች መካከል ጠብ ነግሶ ከነበረ እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል።

ድሽታ ግና ሰላምን እና ፍቅርን ለማውረድ ዓይነተኛ መሳርያ ነው ይላሉ አቶ ዳኜ።

ድሽታ ግና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ፍቅርን እና መግባባትን የሚፈጥር ግጭቶች እንኳ ቢኖሩ በይቅርታ ደም የሚያደርቅ በዓል ነው ሲሉም ያክላሉ።

አሪዎች በታኅሣሥ የበደለን ይቅር ብለው፣ የተጣላን አስታርቀው አዲስ ዓመትን በንፁህ ልብ ከተቀበሉ በኋላ አብሮ በመኖር መካከል ዳግም ጠብ እስኪከሰት ድረስ “ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ፤ ለአራት ለአምስት ወር፤ የተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ቀርተው ሰላም የሚሰፍንበት በዓል ነው” ይላሉ አቶ ዳኜ።

የድሽታ ግናን በዓል የሚያከብሩ ቤተሰቦች ተሰባስበው ሲመገቡ

አዲስ ዓመት ለምን በታኅሣሥ?

የአሪ ምድር ያፈራቸው አዝርዕቶችም ፍሬያቸው ለመሰብሰብ የሚደርሰው ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በመሆኑ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሎንጋ – ታኅሣሥ ምቹ ጊዜ ይሆናል።

በአሪ ደጋማ እና ቆላማ አካባቢዎች አደንጓሬ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ የተለያዩ ስራ ስሮች የሚደርሱት በዚህ ወቅት ነው።

በዓመት ውስጥ አርሶ የተሻለ ያመረተ፣ ከብት አርብቶ ጥሩ ያለበ፣ ቀፎ ሰቅሎ ማር የቆረጠ ፈጣሪውን የሚያመሰግነው በድሽታ ግና ነው።

ድሽታ ግና በሎንጋ (ታኅሣሥ) ወር የሚከበርበትን ሌላው ምክንያት ለማወቅ የአሪ ብሔረሰብን ወቅቶች እና ወራትን መመልከት ያስፈልጋል።

አሪዎች ወቅቶችን በአራት ይከፍላሉ።

ሐሽን (በጋ)፣ ወሊ (በልግ)፣ በርጊ (ክረምት) እና ሹክሊ (ፀደይ) ናቸው።

ሐሽን እና ወሊ የበረከት እና የደስታ ጊዜ ተደርገው ሲወሰዱ፣ በርጊ እና ሹክሊ በአንጻሩ እጅ የሚያጥርበት፣ ችግር የሚበረታባቸው ጊዜያት ናቸው።

የአሪ ዘመን መለወጫ በታኅሣሥ ወር እንደሆነ የተረጋገጠው በወራት ስያሜ እና ቅደም ተከተል ሲቆጠር በቁጥር የተሰየመው ስድስተኛው ወር፣ ግንቦት – ላ በትክክል የሚገኘው በዚያ ወቅት ላይ በመሆኑ ነው ይላሉ አቶ ዳኜ።

በአሪኛ ላ ማለት ስድስት ሲሆን፣ ሰኔ ወይንም ታብዛ ደግሞ ሰባት ማለት ነው። እነዚህ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ወራት የሚገጥሙት በትክክል ከታኅሣሥ መቁጠር ሲጀመር ነው።

የበርጊ እና የሹክሊ አስቸጋሪ ወቅቶች አልፈው በግብርና ምርት አገር ጥጋብ የሚሆንበት ዝናባማ፣ ብርዳማ እና ጭቃማ የነበረው የጨፈገገ የአየር ሁኔታም ተቀይሮ ፀሐያማ እና ሞቃት የበጋ ወቅት የሚጀምረው በታኅሣሥ ወር በመሆኑ አዲስ ዓመትን ለማክበር ምቹ መሆኑን አቶ ዳኜ ይናገራሉ።

“ሎንጋ ረሃብ አልፏል፤ ወንዝን ተሻግሮ ሄዷል። አሁን የጥጋብ ጊዜ ነው የሚል ትርጓሜ አለው።”

አቶ ታምራት በበኩላቸው የእርሻ ወር አልፎ የሚያርፉበት ወቅትም መሆኑ የአዲሱን ዓመት በዓል ለማክበር ተመራጭ ወር ሆኗል ይላሉ።

የአሪ ብሄረሰብ ባህላዊ ስርዓት መሪዎች
የምስሉ መግለጫ,በአሪ ብሄረሰብ ዘንድ ጎድሚዎች የማኅበረሰቡን ባህላዊ ስርዓት፣ደንቦች የሚፈጽሙ፣ኅብረተሰቡን ከተለያዩ ነገሮች የሚከላከሉ ናቸው።

ዘጠኙ የአሪ ባላባቶች

አሪዎች ባሕላዊ መሪ አላቸው። እነዚህ የብሔረሰቡ ባላባቶች ባቢ በማለት ይጠራሉ።

ባቢዎች የተለያየ ማኅበራዊ ሥርዓቶችን በግንባር ቀደምትነት ይመራሉ።

ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ጎድሚዎች ይገኛሉ። ጎድሚ የማኅበረሰቡን ባህላዊ ሥርዓት፣ ደንቦች የሚፈጽሙ፣ ሕብረተሰቡን ከተለያዩ ነገሮች የሚከላከሉ ናቸው።

ከዚያ በታች ያለው ደግሞ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ወይንም በአሪዎች አጠራር ከይስ ታች ያለው ማኅበረሰብ ነው።

የድሽታ ግና በዓል ከኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ሲከበር በቅድሚያ የሚያከብሩት ከይስዎች፣ ወይንም ሕዝቡ ነው።

በቤተሰብ ደረጃ ሲከበር እያንዳንዱ አባወራ፣ እማወራ፣ ግለሰብ ዓመቱን ሙሉ የደከመበት፣ የዘራውን በደስታ የሚሰበስብበት እና የሚያመሰግንበት፣ ከሌሎች ጋር የሚቃመስበትም ጭምር ነው።

በዚህ ውስጥ ሌላኛው የበዓሉ ዕሴት መረዳዳት ነው ይላሉ አቶ ታምራት። ተሳክቶለት ዓመቱን በሙሉ ትርፋማ የነበረው ሰው ላልተሳካለት ያላቸውን ያካፍላሉ።

በተራው ማሕበረሰብ ዘንድ ያሉ የቤተሰብ መሪዎች ካከበሩ በኋላ ጎድሚዎች ቤት ይከበራል።

አሪዎች የተለያዩ አዝርዕቶችን ዘርተው ከሰበሰቡ በኋላ ቀድመው የብሔሩ ባላባቶች (ጎድሚ) እንዲቀምሱ ያደርጋል።

ከዚያ ቀጥሎ ሌላኛው የብሔረሰቡ አባል (ከይስ) እንዲቀምሰው የሚደረገው።

የአካባቢው የእህል ማቃመሱ ሥርዓትም ዝም ብሎ አይከናወንም። በአካባቢው ታላቅ የሆነው ግለሰብ ቀድሞ መቅመስ ይኖርበታል።

ዓመት ሙሉ የተደከመበት አዝርዕት ወደ ቤት ሲገባ ከባላባት ጀምሮ የእህል ማቃመስ ሥርዓቱ መካሄዱ ተረጋግጦ የቤቱ አባወራ በቅደሚያ ቀምሶ ለሌሎቹ ያቃምሳል ይላሉ አቶ ዳኜ።

ይህ ዋናው በዓል ሊከበር አምስት ቀናት ሲቀሩት ከኅዳር 25 እስከ 28 ድረስ የሚከናወን ሲሆን፣ የቤተሰብ መሪዎች፣ ቶይዲ ወይንም ባይራዎች ወደ ጎድሚዎች በመሄድ ያከብራሉ።

ታኅሣሥ 1 የሚከበረው ዋናው የድሽታ ግና በዓል በብሔረሰቡ ባላባቶች፣ ባቢዎች ቤት ነው።

አሪዎች ዘጠኝ ባላባቶች አሏቸው። ዘጠኙ ባላባቶች የራሳቸው የግዛት ክልሎች አሏቸው።

በዘጠኙ ባቢዎች ስር የሚገኙ ባህላዊ ሥርዓት ፈጻሚዎች፣ ጎድሚዎች የድሽታ ግና በዓል በድምቀት እንዲከበር ያደርጋሉ።

እያንዳንዱ አሪ በባላባቱ መኖርያ አካባቢ ወይንም ለበዓሉ ማክበሪያ በተመረጠው ስፍራ ከልጥ እና ከቃጫ የተሠሩ ባህላዊ ልብሶቹን ለብሶ፣ የበደለውን ይቅር ብሎ፣ ከጥጥ የፈትል ከሚሠራ ቲሪዛ ተውቦ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የባህላዊ አልባሳት በፋብሪካ ምርቶች የተተኩ በመሆናቸው ልብሶቹ ስድስት ቀለማት ያሏቸው የማኅበረሰቡ መታወቂያ መሆናቸውን አቶ ዳኜ ይናገራሉ።

አሪዎች በዓሉን ሲያከብሩ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችን ይጫወታሉ።

ወቅቱ በጋና ሥራ የማይበዛበት ስለሆነ ወጣቶች ሌሊት ሌሊት ቡክ (የምሽት ጭፈራ) ወጥተው በዘፈን እና በጭፈራ ይዝናናሉ፤ ቀየውም ያደምቃሉ።

‘ቤሪ’ እየተበላ እየተጠጣ ቁጭ ባሉበት እያዜሙ የሚጫወቱት ሲሆን፣ መጨፈር የሚፈልጉ ወንዶች እና ሴቶች ሁለት ሁለት ሆነው በመነሳት ይጨፍራሉ።

በተለይ ሴቶች ቤሪ መጫወት ላይ የሚያክላቸው የለም ይላሉ አቶ ዳኜ።

በባህላዊ ጭፈራዎች ወቅት ፈጣሪ ይመሰገናል፣ ጎበዝ አራሽ፣ ለጋሽ እና ጀግና ይሞገሳል።

አሪዎች በባላባታቸው ግዛት በጎድሚዎቻቸው እየተደራጁ እየበሉ እየጠጡ፣ ወጣቶች ቆመው ክብ ሰርተው የሚጨፍሩት ደግሞ ‘ወያ’ ይሰኛል።

በዓሉ በሚከበርበት መስክ ላይ ወጣቶች ተቃቅፈው የሚጨፍሩት ደግሞ ‘ዱትሌ’ ይባላል።

ወጣቶች የተለያዩ ባህላዊ ስፖርት ውድድሮችን (ሙክሚ፣ ዣቅሚ፣ ዶብሚ፣ ማንጋ፣ ሃዝሚ) የሚዘወተሩትም በዚሁ በበጋ ወቅት ነው።

አሪዎች የድሽታ ግና በዓልን ሲያከብሩ የተለያዩ ዘፈኖችን እየዘፈኑጭፈራዎችን  ይጨፍራሉ።
የምስሉ መግለጫ,በባህላዊ ጭፈራዎች ወቅት ፈጣሪ ይመሰገናል፣ ጎበዝ አራሽ፣ ለጋሽ እና ጀግና ይሞገሳል።

ንጽህና እና ድሽታ ግና

ድሽታ ግና ፈጣሪን ማመስገን፣ ዕርቀ ሰላምን ማውረድ፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ፍቅር እና አብሮነትን መስበክ፣ እንዲሁም ውስጣዊ እና ውጫዊ ገጽታዎችን ማፅዳት/ማስዋብን ያካትታል ይላሉ አቶ ዳኜ።

እንደ አገር ሽማግሌው ገለጻ ከሆነ አሪዎች ከኅዳር ወር ጀምሮ ተጣልተው እና ተኳርፈው የድሽታ ግናን በዓል በምንም ዓይነት ሁኔታ አያከብሩም።

ባሕላዊ ሥርዓቱ እንዲታረቁ ያስገድዳል። ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ የተጣላም ይታረቃል፣ እንደ ማኅበረሰብም በቡድኖች መካከል ጠብ ነግሶ ከነበረ እርቅ እንዲወርድ ይደረጋል።

አሪዎች በየቤታቸው የሚጠጣ ቦርዴ፣ የሚበላውን በዓይነት በዓይነት ሲያዘጋጁ ሌላም መርሳት የሌለባቸው ነገር መኖሩን አቶ ዳኜ ያስታውሳሉ።

አሪዎች በዓሉ ከመግባቱ በፊት ንጹህ መሆን እንዳለባቸው ያምናሉ።

ይህ ንጹህ መሆን ግን አካባቢን እና ቤትን ከማጽዳት በላይ ነው።

የዲሽታ ጊና በዓል ቂም ተይዞ የሚከበር አይደለም ይላሉ አቶ ዳኜ።

“ለበዓሉ ሲባል በውስጡ ምንም ዓይነት ቂም እና ቅሬታ እንዳይኖር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያጠፋውን ጥፋት በየሠፈሩ እየዞረ ይቅርታ የሚጠይቅበት ጊዜ ነው።”

ሌላኛው ጽዳት እና ውበት የበዓሉ ዕሴት መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑት አቶ ታምራት ይናገራሉ።

አሪዎች ከኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ አዲሱን ዓመት ለመቀበል አካባቢያቸውን ያጸዳሉ። ቤታቸውን በተለያየ ቀለም ያሸበርቃሉ።

በዓሉ የአካባቢም የግለሰብም ንጽህና እንዲኖር ስለሚያስገድድ አዲስ መልበስ፣ ያለውንም አጥቦ ማዘገጃጀት የሥነ ሥርዓቱ አንድ አካል ነው።

ከጽዳት በተጨማሪ የውበት ሥራም የሚከናወን ሲሆን፣ መገለጫውም በተፈጥሯዊ ቀለም ግድግዳን ማስዋብ (ባርትሲ) እና ሴቶች ጉንጫቸው እና ግንባራቸው ላይ የሚነቀሱት ንቅሳት (ዚዕ) ናቸው።

ድሽታ ግና አዲስ ልብስ የሚለበስበት፣ አዲስ ቤት የሚሠራበት እና አሮጌ ቤት የሚታደስበት ጊዜም ነው።

መደጋገፍ፤ የተቸገሩትን በጋራ መደገፍ፣ የደካሞችን ቤት መጠገን፣ የታመሙትን መንከባከብ የዚህ አዲስ ዓመት እሴቶች ናቸው።

ከኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው ይህ በዓል በታኅሣሥ 1 ማጠቃለያውን ያገኛል።

ድሽታ ግና ሲከበር ባቢዎች እና ጎድሚዎች ሲመርቁ አዲሱ ዓመት (ክላ ቦን) የጤና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የበረከት እንዲሆን በመመኘት ነው።

በአሪዎች አፍ “ኡሳ የም ዣዕሼ!” እንኳን አደረሳችሁ ብለናል።