December 9, 2023 – Konjit Sitotaw
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ዋጫሌ ወረዳ፣ ጃቴ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ከሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን አግተው መውሰዳቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።
የቡድኑ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ከዋናው አስፋልት መንገድ ላይ እገታውን የፈጸሙት፣ ረቡዕ’ለት ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ላይ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል።
ሰዎቹ የታገቱት፣ የኦሮሚያ ክልል ታርጋ በለጠፈ በተለምዶ “ሃይሩፍ” ተብሎ በሚጠራ መልስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ሊባኖስ በመጓዝ ላይ ሳሉ እንደኾነ ምንጮች አስረድተዋል።
ታጣቂዎቹ በዚያው ዕለት ሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎችን በኃይል በማገት፣ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሾፌሮችን አፍነው እንደወሰዱም ምንጮች ገልጸዋል። ባካባቢው መሰል የእገታ ድርጊቶች ሲፈጸሙ የአኹኑ የመጀመሪያ እንዳልኾ ዋዜማ መረዳት ችላለች።