
10 ታህሳስ 2023
በቅርቡ ኔትፍሊክስ በባያርድ ሩስቲን ሕይወት ላይ የተመሠረተ ፊልም አውጥቷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ በፕሮዲውሰርነት መሳተፋቸው የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል።
ለብዙዎች ጥያቄ የሆነው ግን ባያርድ ሩስቲን ማን ነው? የሚለው ነው። የአሜሪካንን ታሪክ በሚያውቁ ዘንድም ቢሆን ባያርድ ሩስቲን የሚወሳ ስም አይደለም።
ፊልሙም የተሠራበት ምክንያት ይኸው ነው። ሩስቲን ጥቁሮች ከጭቆና ነጻ ለመውጣት በሚደረገው ትግል ከፍተኛ ሚና ቢጫወትም አስተዋጽው አይነሳም።
በሲቪል መብቶች ንቅናቄ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ሩስቲን በአውሮፓውያኑ 1963 ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘አይ ሃቭ ኤ ድሪም’ (ህልም አለኝ) የሚለውን ንግግር ያደረገበትን የዋሽንግተኑን ሰልፍ ካዘጋጁት መካከልም አንዱ ነው።
ምንም እንኳን የነጻነት ታጋዩ የማርቲን ሉተር ኪንግ ስም፣ እንዲሁም ንግግሩ በመላው ቢናኝም የሩስቲን ስሙ እንኳን አይጠቀስም።
ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ሩስቲን በግልጽ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኑን በመናገሩ ነው። ጉዳዩ በወቅቱ በአሜሪካ የአደባባይ ምናብ ውስጥ ነውር እና አወዛጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ሩስቲንን ለድብደባ ዳርጎታል። ድብደባም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ እንግልት ደርሶበታል፤ ታስሮም ነበር።
በባራክ እና ሚሼል ኦባማ ፕሮዲውሰርነት እንዲሁም በኮልማን ዶሚንጎ መሪ ተዋናይነትም በሩስቲን ሕይወት ላይ የተመሠረተው ፊልም ለዕይታ በቅቷል።
- ኢትዮጵያውያን ‘የሌሉበት’ ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም26 ነሐሴ 2019
- “ሳሊን ፍለጋ”- የዚያ ትውልድ አሻራ ሲገለጥ17 ጥር 2021
- ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ በሂሩት አባቷ ማነው? ስንመለከት23 ጥር 2022

መሪ ተዋናዩም በፊልሙ ባሳየው ድንቅ ችሎታ በፊልሙ ዘርፍ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የኦስካር ሽልማት ያሸንፋል ተብሎም እየተጠበቀ ይገኛል።
በፊልሙ ላይ በመሳተፉም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማውም ተዋናዩ ዶሚንጎ ለቢቢሲ ተናግሯል። ተዋናዩ ኦስካር ያሸንፋል የተባለውን ፊልም ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪ ሌላኛውን ፊልሙን ለማስተዋወቅ ለንደን ይገኛል።
ከቢቢሲ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ በፊት በነበረው ምሽት ‘ዘ ከለር ፐርፕል’ የተሰኘ መጽሐፍን ድጋሚ ወደ ፊልም በለወጠው የዩናይትድ ኪንግደም የፊልሙ ምርቃት ላይ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ታድሞ ነበር።
በዚህ ፊልም ላይ ተዋናዩ ሚስቱን የሚደበድብ እና አስፈሪ ገጸ ባህርይን ተላብሶ ይጫወታል። የቢቢሲ ጋዜጠኛም በምርቃቱ ላይ መገኘቱን በነገረው ወቅት “እዚያ ነበርክ? እናም አሁን አልፈራኸኝም?” ሲል ዶሚንጎ ቀልዷል።
ከከለር ፐርፕል በተለየ በሩስቲን ፊልም ላይ ዶሚንጎ ተወዳጅ፣ ግርማ ሞገስ የተጎናጸፈ እና መሪነት የተላበሰውን የመብት ተሟጋችን ወክሎ ነው የሚተውነው።
በርካታ ተመልካቶች የሩስቲንን ታሪክ ካለማወቃቸው ጋር ተያይዞ ታሪኩ መነገሩ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ዶሚንጎ ይናገራል። ፊልሙ ሩስቲን የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።
ሩስቲን ተብሎ በአጭሩ ርዕስ መሰጠቱ “ጥያቄን ያጭራል። እሱ ማን ነው? ብለው እንዲጠይቁ ያደርጋል” ሲልም ተዋናዩ ይናገራል።
የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ በመሆኑ ምክንያት ከታሪክ መጽሐፍት እንዲፋቅ የተደረገው የመብት ታጋዩ ታሪክ በዓለም ላይ በ238 አገሮች ለዕይታ መብቃቱ ድንቅ መሆኑንም ዶሚንጎ ያስረዳል።
“የዋሽንግተኑ ሰልፍ ዋነኛው ቁልፍ ሰው እና መሐንዲስ ነበር። ዘመቻውን በማደራጀት እና በመቀየስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በእኛ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ትልቅ ተጽእኖን ማሳረፍ የቻለ ሰው ነበር” ይላል።
አክሎም “ከታሪክ መዛግብት እንዲሰረዝ ተደርጎ ነበር። አሁን ከጋረደው ጥላ አውጥተን ታሪኩን እና ማንነቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ ማሳየት ችለናል” ብሏል።
ምንም እንኳን ተቺዎች ስለ ፊልሙ አንዳንድ ቅሬታዎችን ቢያቀርቡም ሁሉም ያለማቅማማት የሚስማሙበት ጉዳይ፣ የዶሚንጎ ድንቅ የትወና ብቃትን ነው።
ኒውዮርክ ታይምስ እና ጋርዲያንን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ዶሚንጎ ከስድስት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረውን የታሪክ ሁነት በአስገራሚ ችሎታ በመተወኑ አወድሰውታል።
ፊልሙ በጆርጅ ሲ ወልፍ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዶሚንጎ በተጨማሪ ክሪስ ሮክ፣ ሲሲኤች ፓውንደር፣ ዳቪን ጆይ ራንዶልፍ እና ጄፍሪ ራይትን የመሳሰሉ ታዋቂ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

የመብት ተሟጋቹ ባያርድ ሩስቲን ማን ነበር?
- በአውሮፓውያኑ 1912 በፔንሲልቬኒያ የተወለደው ባያርድ ሩስቲን ያደገውም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት የአምላክ መገለጫ ነው ብለው የሚያምኑት እና ከክርስትና እምነት አንዱ የሆነው ኩዌከር በተሰኘው እምነትም ውስጥ ነው። ሰላማዊ ተቃውሞን በመስበክም ይታወቃል።
- ከነጻነት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጋር የጠበቀ ጓደኝነት የነበራቸው ሲሆን፣ በሞንትጎምሪ የአውቶብስ አንሳፈርም የተቃውሞ እንቅስቃሴም ላይም ቁልፍ አማካሪው ነበር።
- በአሜሪካ ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በሚወገዝበት እና ጥላቻ በነገሰበትም ወቅት በግልጽነት ይናገር የነበረ እና ማንነቱንም ያልደበቀ ሰው ነበር።
- ሩስቲን በሲቪል የመብቶች ተቃውሞ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የዋሽንግተኑን ለሥራ እና ለነጻነት የተደረገውን ዘመቻ በማዘጋጀት ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ሰዎች መካከልም አንዱ ነው።
- ሰልፉን ለማቀድ እና ለማደራጀት እንዲረዳውም በርካታ ወጣት ተሟጋቾችን አሰባስቦ ነበር።
- በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 28/1963 የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ 250 ሺህ ሕዝብ የተሳተፈበት ሲሆን፣ ይህም ከተጠበቀው በላይ ነበር።
- ሩስቲን በሰልፉ ላይ ተቃዋሚዎች ያላቸውን ጥያቄም በመድረኩ ላይ ያነበበ ሲሆን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ‘አይ ሃፍ ኤ ድሪም’ ንግግሩን ሲያደርግ ከጎኑ ቆሞ ነበር።
- ይህ ሰልፍ የአሜሪካ መንግሥት ለሲቪል መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ያደረገ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 1964 ለጸደቀው የሲቪል መብቶች እና በቀጣዩ ዓመት 1965 ለወጣው የምርጫ መብቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሩስቲን በ75 ዓመቱ በአውሮፓውያኑ 1987 ነበር ሕይወቱ ያለፈው።

ተዋናዩ በመብት ታጋዩ ሩስቲን ታሪክ ላይ የተመሠረተውን ፊልም ለመሥራት በርካታ ጽሁፎቹን አንብቧል። በተጨማሪም ንግግሮቹን ያካተቱ ጥናታዊ ቪዲዮዎችንም ተመልክቷል።
“የንግግሩን ቅላጼ የተረዳሁት በዚህ ወቅት ነው። አቀማመጡን፣ ሲናገር እጆቹን የሚያንቀሳቀስበት መንገድ እንዲሁም አጠቃላይ ባህሪዩን ለመረዳት ችያለሁ። ዋናው ነገር እሱን ማስመሰል ሳይሆን መንፈሱን መጨበጥ ነው” ብሏል ተዋናዩ።
ከፊልሙ ጀርባ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ሚሼል ኦባማ የፕሮዳክሽን ኩባንያ የሆነው ሃየር ግራውንድ አለ። ሩስቲን ከሞተ በኋላም ባራክ ኦባማ ናቸው በአውሮፓውያኑ 2013 ለመብት ተሟጋቹ ፕሬዝዳንታዊ የነጻነት ሜዳሊያ የሸለሙት።
“በእርግጠኝነት ማኅበረሰቡ እንደሚያገለው እያወቀ፣ ከሥራ ሊባረር እንደሚችል እና እንደሚነቀፍም ተረድቶ ማንነቱን ያልደበቀ እና ራሱን የሆነ ደፋር ሰው ነው” ሲሉም ኦባማ የመብት ተሟጋቹን በማወደስ ተናግረው ነበር።
የኦባማዎች ኩባንያ የተሳተፈበት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያ ፊልማቸው ሲሆን፣ ድንቅ ሥራ እንደሠሩም ተዋናዩ ይናገራል።

“ፊልሙ በጥሩ ሁኔታ እንዲሠራ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ እንዳለ የማረጋገጥ ኃላፊነት ነበረባቸው። የፊልም ጽሁፎቹን እንዲሁም ረቂቆችን ማንበብ ነበረባቸው። ለፊልሙ አዘጋጅ ጆርጅ በየቀኑ ዕለታዊ ማስታወሻ ይሰጡት ነበር። ምን እየሠራን እንዳለን እና እንዴት እየሠራን እንደሆነ ተረድተውት ነበር” ሲል ተዋናዩ ስለ ኦባማዎች አስተያየቱን ሰጥቷል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የፊልሙ ሥራ ተቋርጦበት በነበረበት ወቅትም “በዙም ሰብስበውን አይዟችሁ ቀጥሉ እያሉ ያበረታቱን ነበር” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ፊልሙ በኔትፍሊክስ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ዶሚንጎ በመጪው ጥር የሚደረገውን የኦስካር ሽልማት ያሸንፋል የሚል ግምት ተሰጥቶታል።
“ስለ ፊልሙ እንዲህ መነገሩ፣ እያገኘሁት ያለው ፍቅር ሁሉም ድንቅ ነው። ሽልማቱን አሸንፋለሁ ብዬ ባልወራረድም የንግግሩ ማዕከል መሆን በጣም ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም እውቅና የመሰጠት ያህል ነው” ብሏል።
“ሽልማቱን ባሸንፍ ደስ ይለኛል። ድንቅም ነው። ነገር ግን ለእኔ ብቻ አይደለም። ለሩስቲን ባያርድ፣ ለፊልሙ ሠሪዎች እንዲሁም ለባራክ እና ለሚሼል ኦባማ። ለሁላችንም ደስታ የሚፈጥር ነው” ብሏል።