
10 ታህሳስ 2023, 09:48 EAT
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ግማሹ የጋዛ ሕዝብ በረሃብ እየተሰቃየ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ካርል ስካው እንዳሉት ወደ ጋዛ ሰርጥ የገባው እርዳታ በጣም ጥቂት ብቻ ነው።በመሆኑም ከአስር ሰዎች መካከል ዘጠኙ በየቀኑ መመገብ አይችሉም።
በጋዛ ያለው ሁኔታ የእርዳታ አቅርቦቱን ፈታኝ እንዳደረገውም ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት እና እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስለቀቅ በጋዛ የምትፈፅመውን የአየር ድብደባውን መቀጠሏ የግድ እንደሆነ ገልጻለች።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ሪቻርድ ሄችት ቅዳሜ ዕለት ለቢቢሲ ሲናገሩም “ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ሞትና ስቃይ ያማል፤ ነገር ግን ምንም ምርጫ የለንም” ብለዋል።
“ በተቻለ መጠን በጋዛ ሰርጥ ለመግባት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው” ሲሉም አክለዋል።
የእስራኤል ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሄርዚ ሃሌቭ በበኩላቸው “ ሽብርተኞቹ እጅ ሲሰጡ እያየን ነው። ይህም ሰንሰለታቸው እየተበጣጠሰ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ስለዚህ ጦሩ ጫና መፍጠር አለበት” በማለት ለወታደሮቻቸው ሲናገሩ ተቀርፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የባይደን አስተዳደር ለእስራኤል ከ106 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ 14 ሺህ የሚሆኑ የታንክ ጥይቶችን የመሸጥ ውሳኔን ያለ ኮንግረሱ ለማሳለፍ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግን ተጠቅሟል።
የሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈፅመው 1 ሺህ 200 ሰዎች ከተገደሉበትና 240 ሰዎች ደግሞ ከታገቱበት የአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ጀምሮ በጋዛ ውስጥ እና ከጋዛ ውጭ ያለው እንቅስቃሴ በጥብቅ የተገደበ ሆኗል።
እስራኤል ለዚህ ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ከጋዛ ጋር የሚያዋስኗትን ድንበሮች በመዝጋት በጋዛ ላይ የማያባራ የአየር ድብደባ እየፈፀመች ሲሆን ይህም ለጋዛ ነዋሪዎች እርዳታ እንዳይገባ አድርጓል።
በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር እንዳለው እስካሁን የእስራኤል ጦር ከ17 ሺህ 700 በላይ የጋዛ ነዋሪዎችን ገድሏል፤ ከእነዚህ መካከል ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።
ወደ ግዛቷ የተወሰነ እርዳታ እንዲገባ ክፍት የተደረገውም በግብፅ በኩል ራፋህ ድንበር ብቻ ነው።
በዚህ ሳምንት እስራኤል ወደ ጋዛ ማለፍ የሚቻልበትን ኬሬም ሻሎም ኮሪደር በሚቀጥሉት ቀናት ለመክፈት የተስማማች ቢሆንም እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነው።ተሽከርካሪዎቹ ወደ ጋዛ ለመሻገር ወደ ራፋህ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
- እስራኤል ታጋች ለማስለቀቅ የወሰደችው እርምጃ ከሽፎ አንድ ታጋች መገደሉን ሐማስ ገለጸ9 ታህሳስ 2023
- “በጋዛ ሕይወት እየጨለመብኝ ነው” – በጋዛ ያለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ8 ታህሳስ 2023
- የእስራኤል ጦር የሐማስ ኃላፊ የሆነው የያህያ ሲንዋር መኖሪያ ቤትን መክበቡን አስታወቀ7 ታህሳስ 2023
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተሩ ስካው፣ በዚህ ሳምንት ወደ ጋዛ በተጓዙበት ወቅት እርሳቸውና ቡድናቸው ያልጠበቁት “ስጋት፣ ትርምስ እና ተስፋ መቁረጥ” እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
“በመጋዘኖች ያለውን ግራ መጋባት ፣ እርዳታ በሚሰራጭባቸው ቦታዎች የተራቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን፣ መደርደሪያቸው ባዶ የሆኑ ሱፐርማርኬቶችን፣ የፈነዳ ሽንት ቤት ያላቸው የተጨናነቁ መጠለያዎችን ተመልክተናል” ብለዋል።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ባለፈው ወር ላይ የተደረሰው የሰባት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት የተወሰኑ እርዳታዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ አስችሎ የነበረ ቢሆንም፣በጋዛ ያለውን ፍላጎት ለመሙላት ሁለተኛ የመግቢያ ኮሪደር እንደሚያስፈልግ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
“ በአንዳንድ አካባቢዎች ከአስር ቤተሰቦች ዘጠኙ ምንም ምግብ ባፋቸው ሳይዞር ሙሉ ቀንና ሙሉ ሌሊት ያሳልፋሉ።” ብለዋል ስካው።
በሁለት ግንባር በእስራኤል ጦር የተከበበችው በደቡባዊ ጋዛ የምትገኘው ኻን ዩኒስ ከተማ ነዋሪዎችም ያሉበት ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ ከጥቃት በተረፈው ናስር ሆስፒታል ውስጥ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና እና የቃጠሎ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አሕመድ ሞግራቢ፣ በአካባቢው ያለውን የምግብ እጥረት ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“ ሴት ልጅ አለችኝ። ሦስት ዓመቷ ነው። ሁል ጊዜም ጣፋጮች፣ አፕል፣ ፍራፍሬዎችን እንድገዛላት ትጠይቀኛለች ።እኔ ግን ይህን ማድረግ አልችልም። አቅም ቢስ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ ” ብለዋል።
“ በቂ ምግብ የለም።ሩዝ ብቻ ነው ያለው ። ሩዝ በቻ! ይህን ታምናለህ? በቀን እንዴ ነው የምንመገበው” ሲሉም ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
ኻን ዩኒስ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የእስራኤል የአየር ድብደባዎች ኢላማ ሆናለች። የናስር ሆስፒታል ኃላፊው የሕክምና ቡድናቸው ሞተውና ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከቁጥጥራቸው ውጭ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
እስራኤል የሐማስ መሪዎች ምን አልባትም በመሬት ውስጥ በተሰሩ ዋሻዎች ውስጥ በኻን ዩኒስ ከተማ ተደብቀዋል ትላለች።በመሆኑም የቡድኑን የጦር አቅም ለማጥፋት ቤት ለቤት እና ዋሻ ለዋሻ እየታገለች እንደሆነ ገልጻለች።