
10 ታህሳስ 2023
ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ አድርጎ መመዝገቡን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም ሐረር በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ከተማ ለመሆን ስtእበቃ፤ የሸዋል ኢድ በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበ አምስተኛው የኢትዮጵያ ቅርስ ሆኗል።
ሸዋል ኢድ – የሐረሪዎች ድምቀት
የረመዳን ጾም ለእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ የጾም ወር ነው።
በረመዳን ጾም ወር ማብቂያ ላይ ተጨማሪ ስድስት የጾም ቀናት ያሉ ሲሆን፣ የእነዚህን ቀናት መጠናቀቅን ተከትሎ ነው ሐረሪዎች የሸዋል ኢድ በዓልን የሚያከብሩት።
በሐረሪዎች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ከረመዳን ጋር የተያያዙ አው አባድር ዚያራ፣ በድሪ፣ ሀቲመት እና ሸዋል ኢድ ይጠቀሳሉ።
አው አባድር ዚያራ፣ በድሪ እና ሀቲመት የሚከበሩት በረመዳን ወር ሲሆን፣ የሸዋል ኢድ ግን ኢድ አልፈጥር በተከበረ በሳምንቱ ይከበራል።
በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓልን አንድ ሳምንት አልፎ በሐረሪ ብሔረሰብ ዘንድ የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል ለሐረር በተለይም ደግሞ ለጀጎል አካባቢ ድምቀት ነው።
ሸዋል ኢድ ስድስት ቀናትን ተከትሎ ለመከበሩ አንዱ ምክንያት በእስልምና አስተምህሮ ሴቶች በረመዳን ጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ስለሚያቋርጡ ያጎድሏቸውን የጾም ቀናት ለማካካስ እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑን አቶ ተወለዳ አብዶሽ፣ የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ያስረዳሉ።
ወንዶችም ታድያ ተጨማሪ ‘ትሩፋት ለማግኘት’ ጾሙን አብረው ይጾማሉ።
- ታሪካዊዋን ሐረርና ጀጎልን በምስል15 ህዳር 2017
- የመስቀል በዓልን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው 13 ቅርሶች27 መስከረም 2021
- ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የልዑል አለማየሁን አጽም ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ22 ግንቦት 2023
በዓሉ በሐረሪ ክልላዊ ሕዝባዊ እና ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ጥቅምት 8/1999 ዓ.ም. በአዋጅ በመደንገጉ በሐረሪ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
ሸዋል ማለት የታላቁ የረመዳን ወር ፆም ካለቀ እና ኢድ አል-ፊጥር ኢስላማዊ በዓል ከተከበረ በኋላ የሚገኘው ወር ነው ይላሉ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊው።
ማንኛውም ሙስሊም የረመዳንን ወር ጾም ከጾመ በኋላ ስድስት የሸዋል ቀናት ጾሞችን ጨምሮበት ከጾመ ትልቅ ምንዳ ያገኛል ተብሎ ይታመናል።
ሸዋል ኢድ “የሸዋል ጾም ከተጠናቀቀ በኋላ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በድምቀት የሚከበር በዓል ነው” ሲሉ ያክላሉ።
ሸዋል ኢድ በየትኛው ቦታ ያለ ሰው ወደ ሐረር መጥቶ ከቤተሰቡ ጋር የሚዘያየርበት እና ያላገቡ የሚተጫጩበት ባህል ነው ይላሉ የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ።
ሸዋል ኢድ በሸዋል ወር የሚከበር ልዩ በዓል ሲሆን “ባህላዊ እንጂ ሃይማኖታዊ (ሸሪዓዊ) እንዳልሆነ” ኃላፊው ጨምረው ያስረዳሉ።
ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ይልቅ ባህላዊ ትርክት እና ሥርዓቱ እንደሚያመዝን የሃይማኖቱ አዋቂዎች ይናገራሉ።

በሐረሪ ሸዋል ኢድ የባህል አልባሳቶች የሚወጡበት፣ ያላገቡ ሐረሪዎች በጌጣጌጦቻቸው የሚዋቡበት ልዩ ቀን ነው።
ሐረሪዎች የኖረውን ባህላቸውን አጣቅሰው በዓሉ በተለይ ወጣቶች ውሃ አጣጭ የሚመራረጡበት፣ የተፈላለጉ የሚተጫጩበት መሆኑ ትዕይንቱን ያማረ ያደርገዋል ይላሉ።
የሸዋል ኢድ በዓል ወጣቶች በይበልጥ የሚግባቡበት እና የሚተጫጩበት ብቻ ሳይሆን፣ ባህል እና አኗኗራቸውን የሚያንጸብርቁበት አጋጣሚ እንደሆነም ይናገራሉ።
ከዚህም ተነስተው “የሐረሪ ብሔር ባህላዊ ኢድ” የሚሉትም አሉ።
ሸዋል ኢድ በሐረር በጀጎል ዙርያ ካሉ አምስት በሮች በሁለቱ ማለትም በየረር በር (አርጎባ-በሪ) እና ፈላና በር (አስሱሚይ-በሪ) በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው።
ሐረሪዎች መንፈሳዊም ሆነ ባህላዊ ክዋኔዎቻቸውን ለማድመቅ ከበሮ ይጠቀማሉ።
በዝክሪ ለፈጣሪ ምስጋና ያደርሳሉ። ዝክሪ በምስጋና ግጥሞች የተመላ ነው።
ዝክሪ በሌሎች አካባቢዎች ጋር መንዙማ ከሚባለው ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ሐረሪዎች የሸዋል ኢድን በውብ አልባሳት፣ በዝክሪ እና ደባል (ጭፈራ)፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ ተሰባስበው ያከብሩታል።
በዓሉ በሐረሪዎች ዕድሜ እና ፆታ ሳይወስነው ሁሉም የሚሳተፍበት በዓል መሆኑን የክልሉ የባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ይናገራሉ።
ሊቃውንት እና አባቶች ዱዓ በማድረስ፣ እናቶች በዜማ ዝማሬ እና ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ድግስ በማዘጋጀት እና የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመፈለግ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበት በዓል ነው።
የሸዋል ኢድ ክብረ በዓል አከባበር የሚጀመረው ከዋናው በዓል ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው።
በየቤቱ እንዲሁም ‘አው አቅበራ’ እና ‘አው ሹሉም አህመድ’ በተባሉ የሃይማኖት አዋቂዎች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ ድቤ እየተመታ በታዳሚዎች ጭብጨባ በሚታጀብ እና በአዋቂዎች በሚከወን ዝክሪ (መንዙማ) ፈጣሪን በማመስገን ይከወናል።
በሸዋል ኢድ ዱዓው ዝክሪው ብቻ አይደለም የሚሰማው። ባህላዊ ምግብ እና መጠጥም የበዓሉ አንዱ አካል ነው።
በበዓሉ ከሚዘወተሩ ምግቦች መካከል አቅሌል፣ ሐሸር ቃሕዋ፣ ቁጢ ቃሕዋ ይጠቀሳሉ።
አቅሌል፣ በቀይ ወጥ የተዘጋጀ ፍትፍት ሲሆን፣ ሐሸር ቃሕዋ እና ቁጢ ቃሕዋ ከወተት ጋር ተፈልቶ የሚጠጣ ቡና እና ሻይ ነው።
በዚህ በዓል የሚታደሙት በሐረር የሚኖሩ ሐረሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የብሔረሰቡ ተወላጅ ያልሆኑ እና በክልሉ የሚኖሩ፣ በመላው ኢትዮጵያ እና ከአገር ውጪ የሚኖሩ ሐረሪዎች ይህንን በዓል ለመታደም መሰባሰባቸው በዓሉ ይበልጥ እንዲደምቅ የራሱን አስተዋኦ እንደሚያደርግ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
የሸዋል ኢድ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሐረር መከበር እንደተጀመረ ይገመታል።

ጥቂት ስለ ሐረር
ሐረር የጥንታዊት ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማሳያ ተብላ ትጠቀሳለች።
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወቅቱ ሐረርን ያስተዳድሯት የነበሩት አሚር ኑር፣ ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል የገነቡት የጀጎል ግንብ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም እኤአ በ2006 የተመዘገበው ይህ ቅርስ በሐረሪ ክልል ውስጥ ከአዲስ አበባ በ525 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ የሆነችው ሐረር በ7ኛው ክፍለ ዘመን መቆርቆሯ ይነገራል።
በጀጎል ግንብ የተከበበችው የሐረር ከተማ አምስት በሮች አሏት።
በጁጎል ግንብ በተከበበችው የሐረር ከተማ በአነስተኛ የመሬት ስፋት በርካታ ጎብኚዎችን ከሚያስተናግዱ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ ናት።
ከ1000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የከተማዋ ታሪክ ቅርሶቿም እንዲበዙ ዕድል ፈጥሮላታል።
የጀጎል ግንብ እና አምስቱ በሮች፣ የወርቅ ሳንቲሞች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ መስጊዶች፣ የሥነ ሕንፃ፣ የታሪክን አሻራ የሚያንፀባርቁ የቤት ውስጥ ዕቃዎች ቱሪስትን ከሚስቡት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
ሐረር ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና ከመሃል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ አገራት ጋር በንግድ መንገዶች ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባሕር ወደቦች አማካኝነት ትገናኝ ነበር።