
10 ታህሳስ 2023, 08:41 EAT
ቱርክ ሞተረኛውን ገጭቶ ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት ሆኗል ባለችው የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ልጅ ላይ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ አወጣች።
ሞተረኛው አደጋው ከደረሰበት ከስድስት ቀናት በኋላም ሕይወቱ አልፏል።
የፖሊስ ሪፖርት የሚያሳየው የፕሬዚዳንቱ ልጅ መሐመድ ሐሰን ሼክ መሐመድ በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ከሞተረኛው ጋር መጋጨቱን ነው።
ግጭቱ የተፈጸመው በቀን እንደሆነ ያተተው ሪፖርቱ መሐመድ በወቅቱም በኢስታንቡል የሚገኘውን የሶማሊያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ንብረት ነው የተባለውን መኪና እየነዳ እንደሆነም አስታውቋል።
ቱርክ በፕሬዚዳንቱ ልጅ ላይ የጉዞ እገዳ ብትጥልም ቀድሞ ከአገሪቱ ለቆ እንደወጣ ባለስልጣናቱ ያምናሉ።
የኢስታንቡል ከንቲባ ኢክሬም ኢማሞግሉ ከ10 ቀናት በፊት የተከሰተውን አደጋ የሚያሳየውን የደኅነንት ካሜራ (ሲሲቲቪ) የተቀረፀ ቪዲዮ በኤክስ ገጻቸው አጋርተዋል።
ቪዲዮው በተጨናነቀ ጎዳና መገናኛ ላይ አንድ መኪና የሞተር ሳይክሉን ጀርባ ሲመታ ያሳያል።
ሞተረኛው የ38 ዓመት እድሜ ያለውና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዩኑስ ኤምሬ ጎከር ከደረሰበት አደጋ በኋላ ሆስፒታል ቢወሰድም ከስድስት ቀናት በኋላ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ አልፏል።
- ኦባማዎች በፊልም ሥራው የተሳተፉበት ‘ሩስቲን’ ማን ነው?10 ታህሳስ 2023
- ሸዋል ኢድ – ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የሐረሪዎች የአደባባይ በዓል10 ታህሳስ 2023
- ‘የጠፉ መጽሐፍት አዳኙ’ ኤልያስ ሜክሲኮን እስከ ወዲያኛው ይሰናበታት ይሆን?10 ታህሳስ 2023
የመጀመሪያው የፖሊስ ሪፖርት ሞተረኛው ጥፋተኛ በመሆኑ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ከእስር መፈታቱን የሟቹ ሞተረኛ ጠበቃ ለቱርክ ሚዲዎች ተናግረዋል።
ነገር ግን አደጋውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ከተገመገሙ በኋላ ሁኔታው ሌላ ነው ተብሏል። የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ልጅ የሆነው መሐመድ እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።
ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣውም በቱርክ አቃቤ ሕግ በኩል በዚህ ሳምንት አርብ ዕለት ወጥቷል።
የእስር ማዘዣው የወጣው ፖሊስ ወደ ፕሬዚዳንቱ ልጅ ቤት በሄደበት ወቅት ለአንድ ሳምንት ያህል አለመምጣቱን ካወቀ በኋላ መሆኑንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የአገር ውስጥ ዘገባዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ቱርክ እና ሶማሊያ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈው አስር አመት የተጠናከረ ሲሆን፤ ቱርክ በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ ወታደራዊ ስልጠና እና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሶማሊያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች።