ኤልያስ ገብረማሪያም
የምስሉ መግለጫ,ኤልያስ ገብረማሪያም

10 ታህሳስ 2023

ኤልያስ ገብረማሪያም ንባብ በሚያዘወትሩ አዲስ አበቤዎች ዘንድ የሚታወቅ ስም ነው። ዋቢ ሸበሌ ሆቴልን አለፍ እንዳሉ ነጠላ ጫማ የተጫማ ባለ‘ድሬድ’ ፀጉር ጎልማሳ ከተመለከቱ እሱ ኤልያስ ነው።

“ሜክሲኮ አምደ መጻሕፍት” ሲል የሰየማት እና ባለ አስራ አንድ ወለሉን ሸበሌ ሆቴልን ሽቅብ የምትመለከተው የመጽሐፍት መደብሩ ላለፉት አስር ዓመታት ከሜክሲኮ መልኮች አንዷ ነበረች።

ኤልያስ ጋር ተፈልጎ የማይገኝ የድሮ መጽሐፍ አለመኖሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ደንበኞቹ ይገልጻሉ። ከአገርኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራችዎች እስከ ብሉይ (classical) የሩሲያ ልቦለዶች ድረስ ከኤሊያስ መደርደሪያ ላይ አይታጡም። ከዘመን አይሽሬዎቹ የኩራዝ አሳታሚ ውጤቶች እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የአካዳሚ መጽሐፍትም ይገኛሉ።

የማስታወቂያ ሰሌዳ ተጎራብታ የምትገኘው መደብር የመጽሐፍ መሸጫ ብቻ አልነበረችም። “ሜክሲኮ አምደ መጽሐፍት” ከዘመድ ወዳጅ ጋር መገናኛ፣ አዳዲስ ሰው መተዋወቂያም ጭምር ነበረች።

ቦታዋ ይህ ነው የሚባል አካልን ማሳረፊያ ስፍራ ወይም ወንበር የላትም። በጣት የሚቆጠሩ ደንጋዮች ናቸው እንደ ወንበር የሚያገለግሉት። ኤልያስም ሆነ እሱን ብለው የሚመጡ ወዳጆቹ እና ጓደኞቹ የሚቀመጡት በእነዚሁ ድንጋዮች ላይ ነው።

ይህ ወንበር አልባነት የኤሊያስን ወዳጆች በመደብሩ ዙሪያ ሰዓታትን ከማሳለፍ አላገዳቸውም። የኤሊያንስን ቦታ ከሚያዘወትሩት ወዳጆቹ መካከል ደራሲ ኤልሳ ሙሉጌታ አንዷ ናት። “ሐምራዊ ተረኮች” የሚል መጽሐፍ ደራሲዋ፣ ከኤልያስ ጋር ትውውቃቸው የሚጀምረው በ2007 ዓ.ም ነው።

ከዚያ ወዲህ ወዳጅነታቸው እንደቀጠለ ኤልሳ ሙሉጌታ ለቢቢሲ ትናገራለች። ከመጽሐፍ መድብሩ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዷ ኤልሳ ናት።

ኤልሳ ስለመድብሩ ስታወራ፤ “[ሜክሲኮ አምደ መጽሐፍት] መቀጣጠሪያችን ነው። ሰው ‘ሜክሲኮ ነኝ’ ካለኝ ብዙ ጊዜ ኤልያስ ጋር ጠብቁኝ እላለሁ” ትላለች።

ኤልያስ
የምስሉ መግለጫ,ለአላፊ አግዳሚው ክፍት የሆነው የኤልያስ የመጽሐፍት ስብስብ

ኤልያስ (Mexico Book Corner) ማን ነው?

ኤልያስ 36 ዓመቱ ነው። ኤልያስ እና ሜክሲኮ የሚባለውን የአዲስ አበባን አካባቢ ለያይቶ ማየት አይቻልም። ከውልደቱ ጀምሮ ኤልያስ እና ሜክሲኮ ለሦስት አስርት ዓመታት አልተነጣጠሉም።

የተወለደው ከሸበሌ ጀርባ፣ ትምህርቱን የጨረሰው ደግሞ ከሸበሌ ወረድ ብሎ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ነው።

ከተግባረ ዕድ በሚካኒካል ኢንጂነሪንግ ተመርቆ ጋራዥ ውስጥ ተቀጥሮ ሠርቷል። የጋራዥ ሥራው ግን ከልቡ አልደረሰም። ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ “ራሴን የማዝበት ሥራ ነበር የምፈልገው” ሲል በወቅቱ የነበረውን ስሜት ያስታውሳል።

ኤልያስ ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት የጋራዥ ሥራውን ካቆመ በኋላ ያመራው ወደ መጽሐፍ መደርደሪያው ነው። ኤልያስ ሊያነባቸው የገዛቸው 40 መጽሐፍት ተደርድረዋል።

በ20ዎቹ አጋማሽ የነበረው ጎረምሳው ኤልያስ ለንግድ ሳይሆን ለንባብ የገዛቸውን መጽሐፍቶች ይዞ ወደ መንገድ ወጣ። “ድንገት አርባ መጽሐፍት ነበሩኝ በቃ ይዣቸው ወጣሁኝ” ሲል ከአሥር ዓመት በፊት የደረሰበትን ውሳኔ ያነሳል።

“ሜክሲኮ አምደ መጽሐፍት (Mexico Book Corner)” ሲል የሰየማትን የመጽሐፍት መደብርን ከፈተ። ለሽያጭ ይዟቸው ከወጣቸው መጽሐፍት መካከልም በ45 ብር የገዛውን የአዳም ረታን “ግራጫ ቃጭሎች” በ40 ብር እስካሁን ለሚያስታውሳት ሰብለ ለተባለች ደንበኛው ሸጠ።

ይህ ግብይት ለኤልያስ የሚታመን አልነበረም። “ስወጣ ሰው ይገዛኛል ብዬ ጠብቄ አልነበረም” ይላል። ከግራጫ ቃጭሎች ሽያጭ በኋላ ግን ‘ራሳታው’ ኤልያስ እና መጽሐፍቱ የዋቢ ሸበሌ ጎረቤት የሜክሲኮ መልክ ሆኑ።

የጠፉ መጽሐፍትን የሚሹ አንባቢያን ከሚያዘወትሯቸው መደብሮች መካከል የኤልያስ “ሜክሲኮ አምደ መጽሐፍት” አንዱ ነው።

የኤልያስ ደንበኛ እና ወዳጅ የሆነቸው ጽጌሬዳ ጎንፋ “እሱ ጋር የለም የሚባል መጽሐፍ የለም። ገበያ ላይ በቀላሉ የማናገኛቸው መጽሐፍት እሱ ጋር እንኳን ባይኖር ከየትም፣ ከየትም ብሎ ያመጣል” ትላለች።

ኤሊያስ ከአበባ ባልቻ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ኤልያስ ከመንገድ ዳር ሱቁ ባሻገር ለ12 ጊዜ አንባቢና መጽሐፍትን ያሚያገናኝ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቷል

መጽሐፍት አዳኙ ኤልያስ

መጽሐፍት ምን ከገበያ ቢጠፉ ከኤሊያስ ግን ሊሰወሩ አይቻላቸውም። “መጽሐፍ እግር አለው” የሚለው ኤልያስ መጽሐፍትን በተለያ መንገድ እንደሚያገኛቸው ይገልጻል። መጽሐፍ ፍለጋ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ክልል ድረስ ተጉዟል።

ከሁሉም በላይ ግን ሰው ቤት ሄዶ መጽሐፍ መግዛት “በጣም አስደሳች ነው” ይላል። መጽሐፍ ቤታቸው ድረስ ሄዶ ከገዛቸው ግለሰቦች መካከል፤ ጋሽ ወንድሙ ነጋሽ ደስታ አንዱ ናቸው። ጋሽ ወንድሙ ተርጓሚ ናቸው። የዊልያም ሼክስፒርን ሥራዎች ወደ አማርኛ ተርጉመዋል።

አንድ ቀን ጋሽ ወንድሙ ወደ ኤልያስ መደብር ጎራ አሉ፤ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ያገኟቸውን ኤልያስ እና ጓደኞቹን “ኑ ለሰዎች መጽሐፍቶቼን ላስተላልፍ። ብር አልቸገረኝም ከፈለጋችሁ ግን ትገዙኛላችሁ” ብለው ወደ ቤታቸው ወሰዷቸው። ኤሊያስ “ጋሽ ወንድሙ ቤት በመጽሐፍ የተሞላ ግድግዳ ነው የጠበቀኝ” ይላል።

ኤልያስ እና ጓደኞቹ ከተርጓሚው የመጽሐፍት መደርደሪያ ላይ ቀልባቸው ያረፈባቸውን መጽሐፍት ይዘው ወጡ። መጽሐፍቱን “ለሰዎች አስተላለፍን እንጂ ገዛን አንልም” ሲል ይናገራል።

ኤልያስ ላለፉት አሥር ዓመታት መጽሐፍትን ከግለሰቦች እየገዛ ለአንባቢያን በመሸጥ ላይ ቢገኝም “እራሴን እንደ ነጋዴ አልቆጥርም” ባይ ነው። ይህ አስተያየት የእሱ ብቻ ግን አይደለም።

በደንበኞቹም ዐይን ኤልያስ “ነጋዴ” አይደለም። ይህን ሀሳብ ከሚጋሩት ግለሰቦች መካከል ሱራፌል አየለ አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያኑን ሱራፌል እና ኤልያስን ያስተዋወቃቸው ሩሲያዊው ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ ነው።

ከዓመታት በፊት ሱራፌል የሊዮ ቶሊስቶይ ብሉይ ልቦለድ “አና ካረኒና” ኤልያስ ጋር እንደሚገኝ ሰምቶ ወደ ሜክሲኮ ያቀናል። ኤልያስም አላሳፈረውም የቶልስቶይን መጽሐፍ በ200 ብር ሸጠለት። “በወቅቱ ለመጽሐፍ 200 ብር ውድ ዋጋ ነበር” የሚለው ሱራፌል የተጠየቀውን ገንዘብ ለመክፈል ግን አላቅማም።

ሱራፌል እና ኤልያስ ገዢ እና ሻጭ ሆነው ቢተዋወቁም ሱራፌል ግን “ኤሊያስን እንደ ነጋዴ ተመልክቼው አላውቅም” ይላል። “በእኔ እምነት ኤልያስ እየሠራ ያለው የነፍስ ሥራ ነው ብዬ ነው የማስበው” ሲል ያክላል።

ለደንበኞቹ የኤልያስ አንባቢነት ከነጋዴነቱ ያይላል። የሚሸጣቸውን መጽሐፍት ኤልያስ ያውቃቸዋል። አንብቧቸዋልም። ጽጌሬዳ “ኤልያስ አንባቢ ነው፣ ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ስንፈልግ መጽሐፍ የሚሹጡት ሰዎቸ የመጽሐፍቱን ይዘት አያውቁትም። ዋጋም የሚቆርጡላቸው በእጃቸው ከሚይዙት ወረቀት ተነስተው ነው፤ እሱ [ኤልያስ] ግን መጽሐፍትን ስለሚያወቃቸው፣ ስለሚያነባቸውም ጭምር ዋጋቸውን ያውቃል” ስትል ታስረዳለች።

ኤልያስ ጋር ያቀና አንባቢ ስለ መጽሐፍ አውርቶ፣ ተወያይቶም እንጂ መጽሐፍ ገዝቶ ብቻ አይመለስም።

ኤልያስ ይህን ሥራ ከጀመረ ከስድስት ዓመታት በኋላ ከአራት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፤ አንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል። ውሳኔው ከዚህ ሥራ መውጣት እንደማይችል ያስገነዘበው ነበር። ኤሊያስ ሥራውን ሲገልጽ “ሕይወቴ ነው ከዚህ ውስጥ ልወጣ እንደማልችል የወሰንኩት የዛሬ አራት ዓመት ነው” ይላል።

ኤልያስ ከሜክሲኮ ሱቁ እንዲለቅ ከታዘዘ በኋላ መጽሐፍቱን እየሸከፈ
የምስሉ መግለጫ,ኤልያስ ከሜክሲኮ ሱቁ እንዲለቅ ከታዘዘ በኋላ መጽሐፍቱን እየሸከፈ

“በአማርኛ የተጻፈው የአስማት መጽሐፍ”

ኤልያስ የአንድ ብላቴና ዕድሜን ባሳለፈበት ጊዜ ለቁጥር የሚያዳግቱ መጽሐፍትን ገዝቷል፤ ለአንባቢዎቹም ሸጧል። ከመጽሐፍት በተጨማሪም መልሶ አይሽጣቸው እንጂ ሰዎች የዕለት ውሏቸውን ያሰፈሩባቸውን ማስታወሻዎች እና መንግሥታዊ ሰነዶቸን ገዝቷል።

አንድ ቀን የአስማት መጽሐፍ የሚፈልግ ሰው ወደ ኤልያስ መደበር ጎራ አለ። ሰውዬው ለኤሊያስ ያቀረበለት ጥያቄ “የአስማት መጽሐፍ አለህ ወይ?” የሚል ነበር። ኤልያስ የአስማት መጽሐፍ ባይኖረውም መደርደሪያው ላይ ከተቀመጡት መጽሐፍት መካከል ለአስማት ይቀርባሉ ያላቸውን የባህል ሕክምና መጽሐፍትን አሳየው።

ግለሰቡ ግን የሚፈልገውን መጽሐፍ ኤልያስ ካሳየው መጽሐፍት መካከል አላገኘውም። ግለሰቡ ደጅ መጠናቱን፣ ኤልያስም ሌላ መጽሐፍ ማሳየቱን አላቆሙም። እስካሁን ግን የተባለው የአስማት መጽሐፍ አልተገኘም።

ኤልያስ ከአስማት መጽሃፍ ፈላጊው ጋር ያለውን ገጠመኝ፤ “እሱ እርግጠኛ ነው፣ ዘመናዊ መጽሐፍ በአማርኛ የተዘጋጀ የአስማት መጽሐፍ መኖሩን። እኔ ግን በእውነት አላውቅም። እስካሁን አግኝቼውም አላውቅም” ሲል ያስታውሳል።

ምናልባት ኤልያስ እስካሁን ለማግኘት ያዳገተው ይህ በአማርኛ ተጻፈ ነው የተባለው የአስማት መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን አይቀርም።

ሜክሲኮ እምብርት ከሚያቀርበው የጠፉ መጽሐፍት ሽያጭ በተጨማሪ ሌሎች መጽሐፍ ሻጮች የተካተቱበት የጠፉ መጽሐፍት ዓውደ ርዕይ ያዘጋጃል። “እግረ መንገድ” የተሰኘ ስያሜ ያለው ዓውደ ርዕይ እስካሁን ለ12 ጊዜያት ያህል ተካሂዷል።

ኤልያስ “ያኖረኛል” የሚለው ሥራው ብቻ ሳይሆን ነፍሱ የሚደረሰትበት የመጽሐፍ ሽያጭ አሁን “ችግር” ውስጥ መግባቱን ይገልጻል። መጽሐፍ መጻፍ፣ ማሳተም እና መሸጥ፤ “ነገሮች ተደራርበው የወረቀት ነገር ገንዘብም ግሽበትም ተደራርቦ ትንሽ ወስብስብ አድርጎታል” ይላል።

ሰዉም የሚገዛው በቀጥታ “ጥቅም አገኝበታለሁ” የሚላቸውን ዓይነት መጽሐፍት መሆኑንም ያክላል። ኤልያስ ጥቅም ተኮር የሚላቸው መጽሐፍት የመንጃ ፈቃድ ማስተማሪያ፣ የምግብ ዝግጅት፣ ስለ እርግዝና እና የመሳሰሉትን መጽሐፍትን ነው።

በዚህ መካከል በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከሳምንት በፊት ሐሙስ ኅዳር 20/2016 ዓ.ም. ለኤልያስ መጥፎ ቀን ነበር። ከቸርቸር ጎዳና በሚጀምረው የእግረኛ መንገድ ማስፋፊያ ምክንያት ኤልያስ በመጽሐፍ የታጨቀችውን መደርደሪያ ሱቁን እንዲያፈርስ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው።

እንደተባለው መደብሩን ለማፍረስ መጽሐፍቱን ወደ ካርቶን መክተት ጀመረ። ኤልያስ የሐሙስ ኅዳር 20 ሌሊትን ያነጋው እንቅልፍ በዐይኑ ሳይዞር ተቀምጦ እንደሆነ ይናገራል።

ከበሰለለ፣ ንዴት እና ቁጭት በተቀላቀለበ ድምጽ የሚያወራው ኤልያስ አሁን መጽሐፍቱን በካርቶን ሸክፎ የአሥር ዓመት ጎረቤቱ ከሆነው ዋቢ ሸበሌ ግድግዳ ጋር አስጥግቷቸዋል። ስለ ሁኔታው የመንግሥት ኃላፊዎችን ማናገሩን የሚገልጸው ኤልያስ “ትንሽ ታገስ” የሚል ምላሽ ማግኘቱን ይገልጻል።

“የእግረኛ መንገዱ ሲጠናቀቅ ወደ ቀድሞ ቦታዬ እመለሳለሁ” የሚል ተስፋ ያለው እና በርካቶችን “እያገለገልኩ ነው” የሚለው ኤልያስ “በምሠራው ሥራ እጠቅማለሁ” ይላል።