December 10, 2023 – EthiopianReporter.com 


የኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር

ማኅበራዊ ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ምርት ማቆሙ ተሰማ

ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ምርት ማቆሙ ተሰማ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: December 10, 2023

የኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ምርት ማቆሙ ታወቀ፡፡

ከሃያ ዓመታት በላይ ቆርኪና ጣሳ በማምረት የሚታወቀው ይህ ፋብሪካ፣ በጣሳ ምርት ላይ የተሰማሩ 33 ሠራተኞችን ከ2016 ዓ.ም. እና ከ2017 ዓ.ም. በሚቀነስ የዕረፍት ጊዜ እንዲወስዱ ተደርጎ በቤታቸው እንዲቆዩ መደረጋቸውን የፋብሪካው ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ይደነቅ እልፍነው፣ ‹‹ፋብሪካው ለተወሰነ ጊዜ ሥራ ያቆመው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፤›› ቢሉም፣ ፋብሪካው ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ማቆሙንና ሠራተኞቹንም እየበተነ እንደሆነ ሠራተኞቹ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

በፋብሪካው የቆርኪ ምርት ላይ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 15 ሠራተኞች የአገልግሎት ክፍያ ተሰጥቷቸው መሰናበታቸውን የገለጹት የድርጅቱ ሠራተኞች፣ የቀጣይ የሥራ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን ማወቅ እንዳልቻሉና ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቆርኪና የጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደ ግለሰብ ከዞረ ጊዜ ጀምሮ የተሻለ ምርት እንደማያመርትና ሠራተኞችንም ቀስ በቀስ ከሥራ ገበታቸው እንዲወጡ ማደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመንግሥት ሥር እያለ ከ140 በላይ ሠራተኞች እንደነበሩት የሚገልጹት ሠራተኞቹ፣ የጊዜ ገደብ ሳይሰጣቸው ከሥራ መሰናበታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን ወደ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሽን (ኢሠማኮ) ለመውሰድ ቀነ ቀጠሮ መያዛቸውን ጠቅሰው፣ ከ15 ሠራተኞች ውስጥ ሁለት የሚሆኑት እስካሁን ድረስ የአገልግሎት ክፍያ እንዳልተሰጣቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመንግሥት ሥር እያለ የተሻለ ምርት በማምረት ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለሐበሻ ቢራ፣ ለሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪና ለሌሎች ድርቶች ምርቶቹን ሲያከፋፍል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በመጀመሪያ አንድ ድርጅት ከስሪያለሁ ካለ ቅድሚያ በመንግሥት ኦዲት እንዲሠራ ከተደረገ በኋላ የሦስት ወራት ጊዜ በመስጠት ማባረር እንዳለበት በመግለጽ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

በወቅቱ የኢንዱስትሪው ባለቤት የሆነው ግለሰብ በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ ሠራተኞችን በመጥራት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ኪሳራ ስለደረሰብኝ የቆርኪ ሠራተኞች ልበትን ነው ማለቱን ገልጸዋል፡፡

በድርጅቱ በበርታ ኤጀንሲ ሥር ሆነው የተቀጠሩ ዘጠኝ ሴት ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውና ‹‹ለምን አትከፍሉንም?›› የሚለውን ጥያቄ ሲያቀርቡ ኤጀንሲው ይክፈላችሁ የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡   

ከዚህ በፊት የቆርኪ ማምረቻ በፈረቃ 700,000 ቆርኪዎች የማምረት አቅም ኖሮት ከጀመረ በኋላ፣ በሒደት 1.4 ሚሊዮን ቆርኪ የማምረት አቅም ከፍ እንዲል ተደርጎ ሲያመርት መቆየቱ ይታወሳል፡፡

መንግሥት በኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ላይ የነበረውን የ75 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በ130 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ሙሉ በሙሉ ይዞታውን ለኩባንያ ማስረከቡ ይታወሳል፡፡