December 10, 2023 – EthiopianReporter.com


ዜና
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ባንክና የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ ላይ የመሠረተውን ክስ አነሳ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: December 10, 2023

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቁሳቁስ ማምረቻና ጥገና ኢንተርፕራይዝ፣ የኦሮሚያ ባንክ አክሲዮን ማኅበርንና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴን ከምርጫ ጋር በተያያዘ፣ በባንኩና በአስመራጭ ኮሚቴው ላይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ አምስተኛ ንግድ ችሎት መሥርቶት የነበረውን ክስ አነሳ፡፡

ኢንተርፕራይዙ ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ክስ የመሠረተ ቢሆንም፣ ሁለቱ ተቋማት ከፍርድ ቤት ውጪ ተነጋግረው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው፣ ኢንተርፕራይዙ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ክሱ እንዲቋረጥ ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ፣ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 278(1) መሠረት ክሱን አቋርጦ መዝገቡን ዘግቷል፡፡

በመሆኑም ጅማ ዩኒቨርሲቲ የቁሳቁስ ማምረቻና ጥገና ኢንተርፕራይዝ፣ የኦሮሚያ ባንክ አክሲዮን ማኅበርና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴ፣ ትናንት ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊያካሂድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲታገድ አቅርቦት የነበረው ክስ ቀሪ ሆኖ ጉባዔው እንደተካሄደ ታውቋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ክስ የመሠረተው የባንክ ሥራ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር መመርያ SSB/71/2019ን በመቃረን ከፍተኛ ድምፅ ያላቸውን የኢንተርፕራይዙን ዕጩዎች ሳያካትት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የጥቆማ ማስታወቂያ በማውጣቱ እንደነበር በዕለተ ረቡዕ ሪፖርተር ዕትም መዘገቡ ይታወሳል፡፡