
Taye Dendea Aredo
ጦርነትን መቃወም አትችሉም…?
ለምን?
በ1966 ከተነሱት ሶስት የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች በለውጡ የተመለሰዉ የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደሆነ በተደጋጋሚ አንስተናል። በሠላማዊ መንገድ መቃወም ወይም መደገፍ ደግሞ የዴሞክራሲ ምሰሶ መሆኑ ይታወቃል። ኢህአድግንም ሠላማዊ ሠልፎችን ሲከለክል የነበረ አምባገነን በማለት ስንከስና ስንኮንን ሰንብተናል። ዛሬ ግን በመስቀል አደባባይ ሠላማዊ ሠልፍ እንዳይደረግ ከልክለናል። የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ ዜጎች በሠላማዊ ሠልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም ይሰጣል። ያልሸፈቱት እንዲሸፍቱና የሸፈቱት ወደ ሰላም እንዳይመለሱ ማለትም ሊሆን ይችላል።
የጦርነት ድጋፍ በተደረገበት ቦታ የጦርነትን ተቃዉሞ በመከልከላችን ለመመለስ የሚከብድ ጥያቄ ሊነሳብን ይችላል። “ሰላምን የሚጠላዉ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ መንግስት ነዉ” በሚል ብንከሰስ መልሳችን ምን ይሆናል? ለሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያቱ “ከህወሀት በላይ እናንተ ናችሁ” ብንባል ምን እንበል? በኦሮሚያና በአማራ ክልል ወንድማማቾችን እያባላ ላለዉ አደገኛ ግጭት ተጠያቂዉ የጦርነት ተቃዉሞን የሚከለክለዉ አካል ነዉ ከተባለስ? የጀግናዉ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር መጠበቅ ሲገባዉ “በሰፈር ግጭት ጠምዳችሁ የሚታደክሙትና ከወንድሞቹ ጋር ደም የሚታቃቡት እናንተ ናችሁ” የሚል ከሳሽ ድንገት ቢከሰት እንዴት እንመልስ?ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ይሰፍን ዘንድ ሲታገሉ የተሰዉትን፥ የታሰሩትንና የተኮላሹትን ጀግኖች ስናስብስ ህሊናችን ምን ይለናል? በለዉጡ ሞቅታ ወቅት “ስናጠፋ ጠይቁን” አላልንምን?
በኔ እምነት ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ፈፅመናል። የነፃነትና የሰላም መርሆቻችንን በመቃረን ፀረ-ሰላም እርምጃ የወሰድን ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲ የከፈለዉን ውድ ዋጋም ኣራክሰናል። ጦርነት እንዲቆምና ሁሉም ወደ ሰላማዊ ትግል መጥቶ ፖለቲካችን እንድሰለጥን ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ዜጎች በሠላማዊ መንገድ ጦርነትን እንዳይቃወሙ የከለከሉትን አካላት ተጠያቂ ማድረግ ይኖርብናል!
ሠላም ለኢትዮጵያ!
