
ከ 5 ሰአት በፊት
በሱዳኗ መዲና ካርቱም በእርዳታ መኪኖች ላይ ‘‘ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት’ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ።
በዚህ ጥቃት ከሟቾቹም በተጨማሪ ሰባት ሰዎችም መቁሰላቸው ተነግሯል።
የእርዳታ መኪኖቹ የቀይ መስቀል አርማ በግልጽ የያዙ መሆኑን ያስታወቀው ተቋሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችንም ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ለመውሰድ ያቀኑ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
በጥቃቱ ከተጎዱትም መካከል ሶስቱ የረድዔት ድርጅቱ ሰራተኞች እንዳሉበትም ነው አለም አቀፉ ቀይ መስቀል የገለጸው።
ጥቃቱንም “አስደንጋጭ እና ዘግናኝ” ሲል ነው ተቋሙ ባወጣው መግለጫ የፈረጀው።
በሱዳን በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተካሄደ ያለው የርስ በርስ ጦርነት ስምንተኛ ወሩን ይዟል።
የሱዳን መጻኢ ፈንታንም ለመቆጣጠር የሱዳን ጦር ኃይል መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ተፋጠዋል።
በርካታ ተቋማት እና አገራት ግጭት የማቆም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ ባያፈራም ኢጋድ ተስፋ ሰጭ ጉዳይ አግኝቻለሁ ብሏል።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም ፊት ለፊት ለመነጋገር ቃላቸውን ሰጥተውኛል ብሏል።
የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እንዲሁም የፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነት አሳይተዋል ብሏል።
- በሱዳን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ያሉት ሁለቱ ጄነራሎች18 ሚያዚያ 2023
- የሱዳኑ ጦር መሪ ምክትላቸውና ተፋላሚያቸውን ጄነራል ከስልጣን አሰናበቱ19 ግንቦት 2023
- የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ታዩ29 ሀምሌ 2023
ጥቃቱ የተፈጸመው እሁድ ዕለት በከተማዋ ምዕራብ በኩል በምትገኘው አል ሻጃራ ሰፈር መሆኑንም ቀይ መስቀል ገልጿል። የእርዳታ መኪኖቺ “ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተጋላጭ ሰላማዊ ዜጎችን” ከመዲናዋ ካርቱም ወደ ዋድ ማዳኒ ለመውሰድም የተዘጋጁ ናቸው ተብሏል።
ዜጎቹን የማስወጣት ዘመቻው ከተፋላሚ ወገኖች ጥያቄ እንዲሁም ትብብር ጋር የሚፈጸም እንደሆነ ያስታወቀው ተቋሙ ሁለቱም ወገኖች የደህንነት ዋስትና ሰጥተው ነበር ብሏል።
የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል የሱዳን ተልዕኮ ኃላፊ ፒየር ዶርብስ ጥቃቱን ‘ተቀባይነት የሌለው” ነው ብለዋል።
አክለውም “የቀይ መስቀል አርማን እያዩ ክብር አለማሳየታቸው አስደንጋጭ ነው። በአለም አቀፉ ሰብዓዊ ህግ መሰረት ሊከበር እንዲሁም ሊጠበቅ ይገባዋል” ሲሉም ነው ያሳሰቡት።
“የዚህ ተልዕኮ ዋነኛ አላማ እነዚህን ሰላማዊ ዜጎች ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ መውሰድ ነበር ነገር ግን በአሳዛኝ ሁኔታ የንጹኃን ህይወት ተቀጥፏል። በዚህ ጥቃት ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው ሰዎች ጥልቅ ኃዘኔን እየገለጽኩ የተጎዱትም ቶሎ እንዲያገግሙ እመኛለሁ” ብለዋል።
ቀይ መስቀል ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ሊወስዳቸው ያሰባቸው ህሙማን፣ ህጻናት፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ታዳጊዎች እና በዕድሜ የገፉ ዜጎችን ነው። እነዚህን ዜጎች የማስወጣት ይህ ተልዕኮ የተሰረዘ ሲሆን የጸጥታው ሁኔታም እንደገና እስኪገመገም ድረስ ይቆያል ተብሏል።