ከዩኬ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው የነበሩት የአፍጋኒስታን ልዩ ኃይል አባላት
የምስሉ መግለጫ,ከዩኬ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው የነበሩት የአፍጋኒስታን ልዩ ኃይል አባላት

ከ 5 ሰአት በፊት

በቁጥር 200 የሚሆኑና ከዩኬ ጎን ተሰልፈው ታሊባንን ሲፋለሙ የነበሩ የአፍጋኒስታን ልዩ ኃይል ወታደሮች ‘ዩኬ ክህደት ፈጸመችብን’ ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።

እነዚህ ወታደሮች ታሊባን መልሶ አፍጋኒስታንን ሲቆጣጠር በዩኬ ጥገኝነት ለማግኘት ከሁለተኛ አገር ሆነው ሲጠባበቁ የነበሩ ቢሆንም ማመልከቻቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

የቀድሞ የዩኬ ጄኔራልና በአፍጋኒስታን ለ12 ዓመት የገለገሉት ሰር ሲቻርድ ባሮንስ ድርጊቱን ‘’የለየለት ክህደት’’ ሲሉ ገልጸውታል።

አገሬ ዩኬ በነዚህ ወታደሮች ላይ የፈጸመችው ተግባር ‘’አሳፋሪ’ ነው ብለዋል።

‘’ከኛ ጎን ተሰልፈው የተዋደቁ ወታደሮችን መክዳት ማለት እንዲሞቱ መፍቀድ ወይም የዕድሜ ልክ እስራት እንዲገጥማቸው መፍረድ ማለት ነው፤ ይህ አሳፋሪ ነው’’ ብለዋል ጄኔራሉ።

በ2021 የወቅቱ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ‘’የነዚህ ልዩ ኃይል ወታደሮች ለዩኬ ያበረከቱት ድጋፍ ወደር የማይገኝለት ነው’’ ብለው ለምክር ቤት ተናግረው ነበር።

ዩኬ እነዚህን ልዩ ወታደሮች ጥገኝነት ለመስጠት እንደማታቅማማ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

ከነዚህ ልዩ የአፍጋን ወታደሮች ሌላ ከታሊባን መምጣት በፊት በልዩ ልዩ የአፍጋኒስታን መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩ ሲቪሎችም ጥገኝነት ሳያገኙ መቅረታቸው ብዙ እያነጋገረ ነው።

ቢቢሲ በኅዳር 2022 ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ የተላከና ለነዚህ 32 የታሊባን መንግሥት ባለሥልጣናት ጥገኝነት እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ተመልክቷል።

በጎምቱ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ አዛዦች ተጽፎ የተረፈመበት ይህ ደብዳቤ አሜሪካ መራሹ ኃይል አፍጋኒስታንን በተቆጣጠረበት ጊዜ በአካባቢ አስተዳዳሪነት፣ በአቃቢ ሕግና ሌሎች ቁልፍ ቦታዎች ሲሠሩ የነበሩና የአሜሪካንና ዩኬን ሠራዊት ሲያግዙ የነበሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ ጥገኝነት እንዲያገኙ ይማጸናል።

ሆኖም እነዚህ 32 የቀድሞ የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት የጥገኝነት ጥያቄያቸው መና ቀርቷል።

ከነዚህ ሲቪሎች ሌላ አሁን ደግሞ 200 የሚሆኑት የልዩ ኃይል ወታደሮቹም በተመሳሳይ ወደ ዩኬ ለመግባት አመልክተው ማመልከቻቸው ውድቅ ተደርጓል።

አሊ በሚል ስም ራሱን የሚጠራው የዚህ ልዩ ኃይል አባል የነበረ አንድ ወታደር ”ዩኬ ክህደት ፈጽማብናለች” ይላል።

አሊ ማመልከቻውን ሲከታተል የነበረው ከፓኪስታን ሆኖ ነበር። ሆኖም ወደ ዩኬ ለመምጣት አስፈላጊውን ሂደት አሟልቶ ላለፉት ረዥም ወራት ቢጠባበቅም በመጨረሻ መጥፎ ዜና ደርሶታል።

“ከዩኬ ወታደሮች ጋር ቀንም ማታም አብረን ነበርን፤ ትከሻ ለትከሻ ሆነን ነው በጦር አውድማ የተዋደቅነው፣ በአንድ ትሪ በልተናል፣ በአንድ ድንኳን አድረናል። አሁን ግን ተክደናል’’ ብሏል ለቢቢሲ።

ይህ ልዩ ኃይል ኮማንዶ 333 በሚል ስም የሚታወቀው ሲሆን በፈረንጆቹ 2003 ላይ የተቋቋ መ ነው።

ፓኪስታን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰነድ የሌላቸውን አፍጋናዊያንን ወደ አገራቸው የመመለስ ዘመቻ ጀምራለች።

አሊ በአንድ ክፍል ውስጥ ተደብቆ እንደሚኖር ለቢቢሲ የተናገረ ሲሆን ወደ ከፓኪስታን ወደ አፍጋኒሰታን እንዳይባረር ተደብቆ መኖርን እንደመረጠ ተናግሯል።

እነዚህ የልዩ ኮማንዶ አባላት ብቻ አይደሉም በዩኬ መንግሥት ‘ተክደናል’ እያሉ ያሉት።

በርካታ በመንግሥት መዋቅር የአሜሪካንና የዩኬን ሠራዊት ሲያግዙ የነበሩ አፍጋናዊያን ተመሳሳይ እጣ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጄኔራል አብዱል ሃዲ ካሊድ የአሜሪካንን ሠራዊት ያገዙ አፍጋኒስታናዊ ሲሆኑ አሁን በአሜሪካ ጥገኝነት አግኝተው እየኖሩ ነው።

በዩኬ ተቀባይነት ስላጡ የልዩ ኮማንዶ አባላት ሲናገሩ ‘’ በፍጹም ዩኬ ይህን ታደርጋለች ብዬ አልጠበኩም። ክህደት ነው የተፈጸመው፤ ሌላ ምን ይባላል?’’ ብለዋል።

ጄኔራሉ ለዚህ ልዩ ኃይል ትጥቅና ስንቅ-ደመወዝን ጨምሮ ስትሰጥ የነበረውና ያደራጀችው ዩኬ እንደነበረች አብራርተዋል።

‘’ይህ ለምዕራቡ ዓለም ስም የሚያጠለሽና መጥፎ ጠባሳ የሚጥል ነው፤’ ከዚህ ወዲህ ማን ምዕራቡን ያምናል?’ ብለዋል፤ ጄኔራሉ።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ‘’መመዘኛዋን የሚያሟሉ አፍጋናዊያንን ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት አድርገናል’’ ያለ ሲሆን እስከአሁን 24ሺህ 600 ወደ ዩኬ መጥተው ጥገኝነት እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግሯል።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አጭር አስተያየት ‘’የጥገኝነት ጥያቄ ዉሳኔዎች በግለሰቦች ማመልከቻ ሁኔታ እንጂ በሥራ ሚና ብቻ አይወሰኑም። “ የሚል ምላሽ ሰጥቷል።