
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በጋዛ ላይ አጠናክራ የቀጠለችው የማያባራ የቦምብ ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነት ዕድሉን እያጠበበው ነው ሲሉ የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።
ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በዶሃ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ኳታር ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ግፊት ማድረጓን ትቀጥላለች።
ኳታር በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ለአንድ ሳምንት የቆየ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ቁልፍ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውታለች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ጦርነቱ እየተፋፋመ ነው” ሲሉ እሑድ ዕለት ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት “በርካታ የሐማስ አሸባሪዎች” እጃቸውን ሰጥተዋል ብለዋል። “መሳሪያቸውን አስቀምጠው ራሳቸውን ለጀግኖቹ ተዋጊዎቻችን አሳልፈው ሰጥተዋል” ሲሉ አክለዋል።
“ይህ የሐማስ ፍጻሜ የመጀመሪያ ነው።”
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን የገለጹት በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እከፋ ባለበት ወቅት ነው።
በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እስከ እሑድ ከሰዓት 18 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃቶች ተገድለዋል ብሏል።
የሐማስ ታጣቂ ክንፍ ለአልጀዚራ በላከው የድምጽ መልዕክት ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ፋታ ነገሮች ተፈጻሚ አንደሚሆኑ ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት እስራኤል ለውውይት እስክትቀመጥ ድረስ ታጋቾች እንደማይለቀቁ ገልጿል።
ቃል አቀባዩ አቡ ኡባይዳ ባስተላለፉት መልዕክት የሐማስ ተዋጊዎች 180 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አውድመዋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸውን የእስራኤል ወታደሮች መግደላቸውን እና በእስራኤል ላይ የሚያደርሱት ጥቃት በመቀጠሉ “ወደፊት የሚደርሰው ጉዳት ይበልጣል” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ፊሊፔ ላዛሪኒ በበኩላቸው በዶሃ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ጋዛ “የምድር ላይ ሲኦል” ሆናለች ብለዋል።
“በእርግጠኝነትም እንደዚህ ዓይነት የከፋ ሁኔታ አይቼ አላውቅም” ሲሉ አክለዋል።
የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሽታይህ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት እስራኤል “ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን በመጣስ እንድትቀጥል ሊፈቀድላት አይገባም” ከማለት ባለፈ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣልባትም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በዌስት ባንክ የሚንቀሳቀሰውን የፍልስጤም አስተዳደርን ወክለው ነው የተገኙት። አስተዳደሩ በጋዛ ከሚንቀሳቀሰው ሐማስ የተለየ ድርጅት ነው።
ስብሰባው በዶሃ እየተካሄደ በጋዛ ደቡባዊ ክፍል ውጊያው ቀጥሏል።
በሰሜን ጋዛ ከነበረው ጦርነት ሸሽተው ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዲሰደዱ የተገደዱ ሰዎች የተጠለሉባት ኻን ዩኒስ ከተማም ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት በእስራኤል እየተፈጸመባት ይገኛል። እስራኤል የከተማዋን እምብርት ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች።
የእስራኤል ከፍተኛ አማካሪ ማርክ ሬጌቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በኻን ዩኒስ “ከባድ ጦርነት” እንደሚኖር ገልጸዋል። ሲቪሎች “ደህንነታቸው ወደ ተጠበቁ አካባቢዎች እንዲሄዱ” አሳስበዋል። የእስራኤል ታንኮች እሑድ አመሻሽ ላይ ከተማዋ መሐል ደርሰዋል።
በከተማዋ የሚኖሩ ሠላማዊ ዜጎች አስከሬን ሲሰበስቡ እና በጦርነት ለተገደሉ የቤተሰቦቻቸው ሐዘናቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

እስራኤል ደህንነታቸው የተጠበቁ አካባቢዎች ስለምትላቸው አካባቢዎች ሁኔታ የተጠየቁት ሬጌቭ፣ አገራቸው የሲቪሎችን ህይወት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።
በጋዛ ያሉ ሲቪሎች በአል-ማዋሲ ወደሚገኘው “ደህንቱ ወደተጠበቀ ዞን” እንዲሄዱ መልዕክት ተላልፎላቸዋል። 8.5 ካሬ ኪሜ ብቻ የሚለካው ቦታው ከለንደኑ ሄትሮው አውሮፕላን ማረፊያ ያነሰ ነው። ጥቂት ህንፃዎች ያሉት አካባቢው በአብዛኛው አሸዋማ ሜዳ እና የእርሻ መሬትን ያቀፈ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲ ረገድ አጋሮቿ ወጥ አቋም እንዲኖራቸው ጠይቃለች።
ኔታንያሁ ለካቢኔያቸው ማብራሪያ ሲሰጡ “በአንድ በኩል የሐማስን መወገድ እየደገፉ እና በሌላ በኩል ደግሞ ሐማስ እንዳይጠፋ የሚያደርገውን የጦርነት ማቆም ጫና ማሳደር አይችሉም” ብለዋል።
ይህን ያሉት 13 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን ውሳኔ ከደገፉ በኋላ ነው። አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውሳኔውን ስትቃወም፣ ዩናይትድ ኪንግደም ድምጸ ተአቅቦ ማድረጓ ይታወሳል።
እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ከአካባቢው አስወጥታ ወደ ግብጽ ለማሰደድ እየጣረች ነው የሚለውን የላዛራኒን ወቀሳ ውድቅ አድርጋለች። እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ሲናይ ለማስፈር እንደምትፈልግ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ያልተለመደ የተባለ እምርጃ በመውሰድ በጋዛ አፋጣኝ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠይቅ ውሳኔ አስተላልፏል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቀደም ሲል በጋዛ ያለውን ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸውታል።