በሱዳን ጦርነት ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል
የምስሉ መግለጫ,በሱዳን ጦርነት ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል

ከ 3 ሰአት በፊት

በሱዳን እየተፋለሙ ያሉት ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያከብሩ መስማማታቸውን ኢጋድ ገለጸ።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) እሑድ እንዳስታወቀው እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰው በጂቡቲ በተደረገ የአባላት አገራት ስብሰባ ነው።

ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመሩት ኃይል የፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ጀምሮ ሲፋለም ቆይቷል።

በዚህ ጂቡቲ በተደረገው ጉባኤ አብዱልፈታህ አልቡርሃን ተገኝተዋል። የኢጋድ መሪዎች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከሚመሩት ጄኔራል ሐምዳን ደጋሎ ጋር በስልክ መነጋገራቸውም ተመላክቷል።

ሁለቱም ጄኔራሎች የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ የተስማሙበት ሲሆን ከዚህ የተኩስ አቁም በኋላ በተናጥል በአካል እንደሚገናኙም ይጠበቃል።

በሚሊዮኖች ያፈናቀለውና ሺዎችን ለሞት የዳረገውን ጦርነትም በፖለቲካ ንግግር መፍትሄ ለመስጠት ሁለቱ ተዋጊ ወገኖች ቃል ገብተዋል።

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ዜና የወጣው አሜሪካ ሁለቱም ወገኖች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ማለቷን ተከትሎ ነው።

ዋሺንግተን የፈጥኖ ደራሹን ኃይልና አጋር ሚሊሻዎቹ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ከሳለች።

በዚህ ጦርነት በሚሊዯን የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።

ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶች የተፈረሙ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ ተጥሰዋል።