ም/ፕሬዝዳንት ፊሊፓ ምፓንጎ
የምስሉ መግለጫ,ም/ፕሬዝዳንት ፊሊፓ ምፓንጎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታመዋል መባሉን አስተባብለው ለሥራ ውጭ አገር እንደነበሩ ገልጸዋል

11 ታህሳስ 2023, 15:14 EAT

ስለ ታንዛኒያ ምክንትል ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ምፓንጎ የጤና ሁኔታ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የተጠረጠሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ በአገሪቱ መሪዎች ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከአንድ ወር በላይ በሕዝብ አደባባይ ሳይታዩ ከቀሩ በኋላ ትላንት በይፋ ታይተዋል።

በይፋ መታየታቸው በርካቶችን እፎይታ ሰጥቷል። ሞተዋል የሚል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር።

የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት ኔፕ ናኙይ ወሬውን ያሰራጩት ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞተዋል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨው ወሬ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታዩት እአአ ጥቅምት 31 ነበር። በዕለቱ የደቡባዊ አፍሪካ አገራት የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰንን ወክለው ተገኝተዋል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ከዕይታ መሰወር ስጋት አጭሮ የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃሲም ማጃሊዋም በዚህ ዙሪያ ሐሰተኛ ወሬ እንዳይነዛ አስጠንቅቀው ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት እሁድ በአገሪቱ መዲና ዶዶማ ተገኝተው ጤነኛ እንደሆኑ እና ክብደታቸው እንዳልቀነሰ ተናግረዋል።

“ፎቶዬ ከሻማ ጋር ሆኖ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ነበር። መሞቴም ተነግሯል። ፈጣሪ የሰጠኝን ሥራ ግን አልጨረስኩም። ወደእሱ የምመለሰው ጊዜው ሲደርስ ነው። ስለፀሎታችሁ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ከሕዝብ ዕይታ የጠፉት “ልዩ ኃላፊነት” ተሰጥቷቸው ስለነበረ መሆኑን ከመግለጽ በዘለለ ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።

ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሰተኛ መረጃ ያሰራጩ ምርመራ እንዲደረግባቸው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አዘው፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጥንቃቄ የተሞላው እንዲሆን አሳስበዋል።

“የሌላን ሰው መብት መጋፋት አያስፈልግም” ብለዋል።

ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሰተኛ መረጃ ሲሰራጭ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

እአአ በ2021 ሞተዋል የሚል ሐሰተኛ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ እህታቸው ራሷን መሳቷን ተናግረዋል።