ዓርማ

11 ታህሳስ 2023, 17:35 EAT

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በአገልግጋዮች፣ በምዕመናን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ነው አለ።

ሲኖዶሱ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 01/2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ላይ በቅርቡ በተለያዩ ስፍራዎች በምዕመናን እና በቤተክርስቲያኗ አባቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በዝርዝር አመልክቷል።

“ግድያና፣ ስደት፣ የንብረት ውድመት እና መፈናቀል” ተደጋጋሚ ክስተት መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ “በወለጋ፣ በጐንደር፣ በጐጃም፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመሳሰሉት እየተፈጸመ ያለው ድርጊት. . . መንግሥት ባለበት አገር ሃይማኖት ተኮር ጥላቻዎች፣ የንፁሐን ሕይወት መቀጠፍ እና ሀብት ውድመት” አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሷል።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በሽርካ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኙ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ በቅርቡ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ በጥቃቶቹ ከተገደሉት መካከል የሰባ ዓመት አዛውንት እና የሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻን ይገኙበታል ተብሏል።

ይህንን ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተመሳሳይ ሪፖርት ባለፈው ሳምንት ያወጣ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽንም ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጦ መንግሥት ሽብርተኛ የሚለው “ሸኔ”፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ አድርጓል።

እንዲሁም በማዕከላዊ ጐንደር አገረ ስብከት አንድ የቤተክርስቲያኗ መምህር “ባልታወቀ ግለሰብ በድንጋይ ተወግረው መገደላቸው” በተጨማሪም የማዕከላዊ ጐንደር ዞን አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በተመሳሳይ “ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተመተው መገደላቸው” መግለጫው ገልጿል።

ሲኖዶሱ እንዳለው እያጋጠመ ባለው በጭካኔ የተሞላ ድርጊት “ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ማጣት የዜጎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት፣ የእምነት ተቋማት፣ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች…” ላይ በቀላሉ የማይመለስ አደጋን እያደረሰ ነው።

ይህ ተደጋጋሚ ክስተት የዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ የአካል እና የንብረት ደኅንነታቸው፣ የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነት ስጋት ላይ ከመጣሉ በሻገር “የዜጎችን ሁለንተናዊ ደኅንነትን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ግዴታ ያለባቸውን አካላት በሙሉ በምድርም ሆነ በሰማይ ተጠያቂ የሚያደርግ ጉዳይ ነው” ብሏል።

በአገሪቱ ረሀብ፣ ድርቅ፣ የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት ካስከተሉት ችግር በተጨማሪ በተፈጠሩት አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች ምክንያት “በርካቶች ቀያቸውን ለቀው፣ መነኰሳት ገዳማትን ትተው ተሰደዋል፤ ወላድ እናቶች፣ ሕሙማን እና አረጋውያን በሕክምና እጦት እያለቁ ነው፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ከጤናማ እድገት እና ከትምህርት ገበታ ተደናቅፈዋል” በማለት አጠቃላዩን ሁኔታ ገልጾታል።

ሲኖዶሱ በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ከእርስ በርስ መገዳደል እና ጦርነት ለመውጣት በውይይት እና በምክክር እንዲደረግ እና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ተግባር ቅድሚያ እንዲሰጠው ለሁሉም ጥሪ አቅርቧል።

እንዲሁም በቤተክርስቲያኗ ምዕመናን እና ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ መንግሥት እና የሚመለከታችሁ አካላት ዋስትና እንድትሰጡ፣ ወንጀል ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ድርጊቱን መላው ዓለም እንዲያወግዘው ቋሚ ሲኖዶስሱ አጥብቆ ጠይቋል።

በተጨማሪም አደጋ ተደቅኖባቸዋል ያላቸው ዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም፣ አሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤል ገዳም እና አካባቢው፣ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምን የመሳሰሉ ታላላቅ አድባራት እና ገዳማት ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስቧል።

ለዚህ ለቤተክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው እና ከሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸው መውደሙን እና በስጋት ምክንያት ከመኖሪያቸው መሸሻቸውን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።