December 11, 2023 

በገደብ ከተማ የጌደኡፋ (Gede’uffa) ቋንቋን ያልተጠቀሙ የተለያዩ የአገልግሎት ማስታወቂያዎችን የማንሳት ስራ እየተሰራ መሆኑ ተሰምቷል።

በጌደኦ ዞን ዉስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የጌደኡፋን (Gede’uffa) ቋንቋ የስራ ቋንቋ እንዲያደርጉና የትኛውም ማስታወቂያ ከላይ በጌደኡፋ እንዲጻፍ መልእክት ተላልፏል።

በዚህ መሰረት በገደብ ከተማ የጌደኡፋን ቋንቋን የማይወክሉ ናቸው የተባሉ የተለያዩ  ማስታወቂያዎችን የማንሳት ስራ እየሰራ መሆኑን የገደብ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ገልጿል።

የገደብ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ አስቴር ምትኬ የጌደኡፋ (Gede’uffa) ቋንቋን የስራ ቋንቋ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ከነዚህም ዉስጥ በአማርኛ ብቻ የተጻፉ ማስታወቂያዎችን በማያነሱ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ እርምጃ  ሳይወሰድ በፊት በመጀመሪያ የቃል ማስጠንቀቂያና ትምህርት በመስጠት ቀጥሎም በአማርኛ ብቻ የተጻፉ ጽሁፎችን  በጌደኡፋ እንዲለወጡ መደረጉን  በተጨማሪም ህግ በማያከብሩ አካላት ላይ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ በመሆን እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የጌደኡፋ ቋንቋ የስራ ቋንቋ መሆኑን በመገንዘብ የትኛውም ቦታ የተጻፉ ጽሁፎች በመጀምሪያ በጌደኡፋ መጻፋቸውን  በማረጋገጥ እና የሚያስችግሩ ጽሁፎችም ካሉ ወደ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በመምጣት እገዛ ማግኘት እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

ይሁንና በከተማዉ ዉስጥ ያሉ አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ሳንዘጋጅና የመቀየሪያ በቂ ጊዜ ሳይሰጥን ታፔላችን ተነስቶብናል በማለት ቅሬታ አቅርበዋል።

ይህን ቅሬታ በተመለከተ አስተያየታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጲያ የሰጡት የገደብ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ መስታዉት አብርሃም ፤ ለንግድ ድርጅቶች የመጠሪያ ስማቸዉ ላይ የጌዲዮ ቋንቋን (Gede’uffa) ለመጨመር ከተሰጠዉ ጊዜ በላይ ቋንቋውን ለማይችሉ አካላት በወረዳዉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል ተጽፎ እስከመሰጠት መድረሱን አሳዉቀዋል።

አሁን ላይ የከተማዉን የንግድ ምልክቶች የስያሜ ቋንቋ ለመቀየር የተቋቋመ ግብረሀይል ስራ ላይ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ መስታዉት ስራዉ ከማህበረሰቡ ጋር በመግባባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ፤ ከጌዲኦፋ ቋንቋ (Gede’uffa) ዉጭ ተከልክሏል የሚባለዉ ዜና ከእዉነት የራቀና ከላይ የጌዲኦፋ ቋንቋ ከተጻፈ ከታች ማንኛዉንም ቋንቋ መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

* አንዳንድ በጌዴኦፋ ቋንቋ የተፃፉ ነገር ግን የፊደል ስህተት ያለባቸውም ማስታወቂያዎች እየተነሱ ስለመሆኑ ታውቋል።

መረጃውን አዘጋጅቶ የላከው የሀዋሳው የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ነው ።

@tikvahethiopia